(በሚኪ አማራ) ኦነጎች እንግዲህ ከረዠም አመት በኋላ ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በእርግጥ የመንግስት ጥሪ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም የአዉሮፓ ብርድ አጥንቴ ዉስጥ ሰርስሮ እየገባ አስቸገረኝ መጥቼ ቀሪዋን እድሜ ልጨርስ እያሉ ሲለምኑ ነበር እነ ሌንጮ፡፡ እኒህ ሰወች አሁንም ፖለቲካ ዉስጥ የመቀጠል ፍላጎት አላቸዉ፡፡ በዚህ እድሜ መቸም ጡረታ ይወጣል ተብሎ ነዉ የሚጠበቀዉ እንጅ ዲሞክራሲ አሰፍናለዉ ምናምን የሚል ከእንደዚህ አይነት ሽማግሌ ለዛዉም 30 አመት ገደማ መሬት ላይ ያለዉን የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እና ሂደት ያላየ እና ያላለፈበት፡፡ቲፒካል የ60ወቹ ትዉልድ ባህሪ ነዉ፡፡ የኦነግ ወደ አገር ቤት መምጣት እና በፖለቲካዉ ዘንድ ለመሳተፍ መፈለጉ ጊዜዉን ጠብቆ አቧራ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ በተለይም የእነ በቀለ ገርባ ድርጅት (ኦፌኮ) አሁን ያለዉን የፖለቲካ ምህዳር ለማምጣት ከኦነጎች በተሻለ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ኦፌኮ በ2012 ስልጣን ከኦህዴድ እንደሚረከብ እርግጠኛ የሆነ ይመስላል፡፡ ቄሮ የሚባለዉ ወጣት ቡድን ኦህዴድ ወርቅ ቢያነጥፍለት ከኦፌኮ አስቀድሞ አይመርጠዉም፡፡ ኦህዴድ በለማ እና በአብይ የተሻለ ቅርጽ ያለዉ ቢመስልም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኦፌኮ ከኦህዴድ በተሻለ ኮንሰርቫቲቭ ሆኖ የመቅረብ እድል አለዉ፡፡ ኦህዴድ ደግሞ መንግስት ስለሆን ሌላዉን ኢትዮጵያዊ እና ሌሎችን ድርጅቶች ላለማስቀየም አብዛኛዉ የኦሮሞ ወጣት የሚፈልገዉን ወደ ኦነግ ያጋደለ የፖለቲካ ትርክት በፓርቲ ዲሲፕሊን ምክንያት ይዞ ላይቀርብ ይችላል፡፡ እነ ሌንጮ ሽማግሌ ቢሆኑም ቅሉ የኦነግ አስተሳሰብ እስካሁንም ድረስ በኦሮሚያ በተለይም በመካከለኛ የጉልምስና እድሜ የሚገኘዉ ማህበረሰብ ላይ በስፋት አለ በተለይም በገጠሩ አካባቢ፡፡ ስለዚህም ኦነግ ምናልባትም የተማሩና ወጣት ፖለቲከኞችን በመመልመል እና በማደራጀት በአጭር ጊዜ ዉስጥ የራሳቸዉን የፖለቲካ ሃይል መመስረት ይችላሉ፡፡ ሶስቱም ድርጅቶች በአላማ ያን ያህል ባይራራቁም ፖለቲካ እና ፓወር እስከሆነ ድረስ በትንሽ ነገርም መፋተግ አይቀርም፡፡ በተለይ ኦፌኮ ትልቅ ህልም ስላለዉ እየታሰሩ እየተፈቱ እዚህ ያደረሱትን ፖለቲካ አዉሮፓ እና አሜሪካ የስታር ባክስ ቡናዉን እየጠጣ ኖሮ ከነሱ እኩል ሲወዳደር ደስተኛ አይሆኑም፡፡
ጃዋርና ኦፌኮ
———-
በቀለ ገርባ ከላይ እንዳልኩት አሁን ያለዉን የተደራጀ የኦሮሞ ወጣት በመጠቀም ኦህዴድን የመገልበጥ ትልቅ ህልም አለዉ፡፡ ለዚህ ዋነኛዉ ሞተሩ ደግሞ ጃዋር ነዉ፡፡ በቀለ ከጃዋር ጋር ይሄን ያህል የቀረበ ግንኙነት ኖሮት አያዉቅም ወይም በቀለ ገርባ ብዙ ጊዜ ከዲያስፖራ ፖለቲከኞች ጋር ጃዋርን ጨምሮ ግንኙነቱ በጥንቃቄ እና ዉስን በሆነች መንገድ ነበር፡፡ አሁን ግን በቀለ ጃዋርን በ 2012 ምርጫ አጥብቆ ይፈልገዋል፡፡ ጃዋርም ከኦነግ ሽማግሌወች ይልቅ ወደ ኦፌኮ የሚያደላ ይመስላል፡፡ ለዛም ነዉ ሰሞኑን ሽር ብትን እያሉ ያሉት፡፡ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጃዋርና በቀለ በደንብ ለኦሮሞ ወጣቶች እባካቹህ እዩን እያሉ ነዉ፡፡ የፕሮሞሽን ስራ እየተሰራ ነዉ፡፡ ምናልባትም ጃዋር ከሁለት አመት በኋላ ወደ ምወደዉ የአካዳሚክስ ሙያ እመለሳለዉ ብሎ ባለፈዉ ጽፎ ነበር፡፡ ይሄም የሚሆነዉ ከምርጫዉ ማግስት ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ የፓርቲ ዲሲፕሊን ሳይገድበዉ በፓርላማም ሆነ በሌላዉ የፖለቲካ ፕላትፎረም ሊያራግቡ የሚችሉ የኦፌኮ ሰወች ናቸዉ፡፡ ከዛም በላይ እነ በቀለ እና ዶ/ር መራራ ተቃዋሚ ስለሆኑ በሌላዉ ኢትዮጵያዊ ዘንድ እራሱ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ከኦህዴዶች በላይ፡፡ ስለዚህም ጃዋር በተቻለ መጠን ኦፌኮ ብዙ የፓርላማ ወንበር ከኦህዴድ እንዲረከብ ይፈልጋል፡፡ ከዛ ብኋላ ጃዋር ምናልባትም ወደ ዶክትሬት ጥናቱ ሊመለስ ይችላል፡፡ትናንት ከድሮ የስታንፎርድ አስተማሪዉ ጋር የታየዉ ምናልባትም የፒ ኤች ዲ ዲግሪ ቅድመ ዝግጅት ይመስላል ወይም ከዚህ በፊት ያቋረጠዉን ለመቀጠል፡፡
ኦህዴድ
——
ኦህዴድ አሁን ባለዉ ሁኔታ ለኦሮሞ ህዝብ ጥሩ እየሰራ ነዉ፡፡ እነ ኦነግም፤ ኦፌኮም ሆነ ጃዋር ያራግቧቸዉ የነበሩ ጥያቄወችን ተቀብሎ ፖለቲካዊ መስመር አስይዞ እየሄደ ነዉ፡፡ ነገር ግን በምርጫ ከመሸነፍ አያድነዉም፡፡ አሁንም ቢሆን ኦህዴድን ብዙዉ ሰዉ የህወሃት ተላላኪ አድርጎ ነዉ የሚያየዉ፡፡ ባይሆንም እንኳን ባለፉት 27 አመታት የሰራቸዉ ስራወች በቀላሉ የሚረሱ አይደሉም፡፡ ዶ/ር አብይንና ለማ መገርሳን እንወዳችዋለን ነገር ግን የምንመርጠዉ ሌሎችን ነዉ ማለታቸዉ አይቀርም፡፡ ኦህዴድ በቀላሉ መሸነፉ አይቀርም በተለይም በከተሞች አካባቢ፡፡ ስለዚህም ኦህዴድ ምናልባትም ባለዉ መዋቅር ብዙን የገጠር አካባቢ ስለሚደርስ ገጠሩ ላይ አተኩሮ ካልሰራ በቀር ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆኑ ከመሸነፍ አያድነዉም፡፡ ሁለት ነገሮች ግን ሽንፈቱን ሊያስቀሩለት ይችላል፡፡ አንደኛ ኦህዴድ የሚለዉን ስምና ባንዴራዉን መቀየር፡፡ ሁለተኛ ምርጫዉ ከመድረሱ በፊት የኦህዴድ Public face ሁነዉ የኖሩትን እነ አባዱላን፤ ደሚቱን፤ ግርማ ብሩን እና ኩማ የመሳሰሉ ሰወችን በጡረታ ማስወገድ፡፡ኦህዴድ ምናልባትም እነ ሌንጮ ፖለቲካዉ ላይ ከማማከር በዘለለ እንዳይሳተፉ ሊደራደርም ይችላል፡፡ እንደዛ ካደረገ ቢያንስ ኦሮሚያ ዉስጥ ሊመጣ የሚችለዉን የምርጫ መከፋፈል ሊቀንስ ይችላል፡፡
ብአዴን
——
ብአዴን እንዲህ አይነት ዉስብስብ ፖለቲካ አይገባዉም፡፡ ዝማም ሆነች ገዱ የአማራ ቴሌቪዠዥንን ዜና ጋቢ ለብሰዉ ቁጭ ብለዉ አይተዉ እግራቸዉን ታጥበዉ ይተኛሉ እንጅ አዲስ አበባ ምን እየተካሄደ እንዳለ እንዴት ያዉቃሉ፡፡ ብአዴን አገር ሰላም ከሆነለትና ባህርዳር የብአዴን ጽ/ቤትን ማንም ካልነጠቀዉ ለምን በደቡብ እስከፍኖተሰላም በሰሜን እስከ ወረታ አይቀራመቱትም፡፡ ዝም ነዉ የሚለዉ፡፡ አሁን ያለዉን የኦሮሞን ፖለቲካ በሚገባ ሚረዳዉ ምናልባትም በረከት ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ነገር ግን በረከት የኦሮሞን ፖለቲካ የሚከታተልበት መነጸር ከብአዴን ወይም ከአማራ ህዝብ አንጻር ሳይሆን ከህወሃት ወይም ከትግራይ ህዝብ አንጻር ዝቅ ሲልም ከራሱ ህልዉና አንጻር ነዉ፡፡ እነ ሌንጮ አማራን ጨፍጭፈዋል በገደልም ከተዋል፡፡ የሚያሳስበዉ ያለፈዉ አይደለም፡፡ ሌንጮን እንደ ሲምቦል የሚያዩ ብዙ የኦሮሞ የመካከለኛ እድሜ አድናቂወች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተወሰንም መልኩ እየቀነሰ መቶ የነበረዉ የኦነግ አስተሳሰብ ማነቃቃቱ እና የዛሬ 27 አመት የተደረገዉ ጭፍጨፋ እንደገና ማገርሸቱ አይቀርም፡፡ በዚህም ምክንያት እዛ ክልል የሚኖር አማራ አደጋ ዉስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ብአዴን ትክክለኛ ተወካይ ቢሆን ኖሮ እንደ ኢህአዴግ አባልነቱ ኦነግ ከዛሬ 27 አመት በፊት ለጨፈጨፏቸዉ አማሮች ተጠያቂ የሚሆንበትን እንዲሁም ወደ ፖለቲካዉ ከገባ በኋላ ያኔ ያደረጉትን እሁን እንዳይደግሙት የድርድሩ አካል እንዲሆን ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ አልሆነም፡፡ ብአዴንን ሲያታልሉት የአማራን ተቃዋሚዎች ተደራድራችሁ አስገቡ እኛ ደግሞ የኦሮሞን ተቃዋሚዎች እናስገባ አሉት፡፡ እነሱ ኦነግን ከአዉሮፓና አሜሪካ ሲያስመጡ ብአዴን አንድ ሰዉየ ከአርማጭሆ በአንድ ሽህ ወታደር አጀብ አድርጎ ጎንደር ላይ ሄዶ አቀባበል አድርጎ መጣ፡፡ ይችዉ ነች የብአዴን አስተሳሰብ እና ችሎታ፡፡
ሀወሃት
—–
ህወሃት ከራሱ ዉጪ የጠነከረ አጋር ፓርቲ ማየት አይፈልግም፡፡ ኦህዴድ እየጠነከረበት መሆኑን ተረድቷል፡፡ ስለዚህም የኦነግ አገር ቤት መግባቱ ከኦህዴድና ከኦፌኮ ጋር ተዳምሮ በተወሰነ መልኩ በአንድነት ወደ ፌዴራሉ መንግስት ዙረዉ የነበሩትን አሁን እዛዉ ኦሮሚያ ዉስጥ ሽኩቻ እንዲኖ ይፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ምናልባትም ኦነግን በመጠቀም አማሮች ላይ ከፍተኛ ጥቃት አንዲፈጸም በማድረግ የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት መሮጡ አይቀርም፡፡ ለህወሃት ኦሮሚያ ዉስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢያሸንፍለት ደስታዉ ነዉ፡፡ የእነ ዶ/ር መራራ ወይም በቀለ ገርባ ድርጅት አሸንፎ ቢመጣ ህወሃት በበላይነት የያዘዉን ደህንነትና ወታደራዊ መዋቅር ተቆጣጥረዉ እዉነተኛ ፓወር ማግኘት አዳጋች ነዉ፡፡እነ ሌንጮ ህወሃትን ከዛሬ 6 አመት ገደማ ጀምሮ ይለምኑ ነበር፡፡ ለዛዉም ፖለቲካ ዉስጥ ላለመግባት ጡረታ ወተዉ አገራቸዉ ላይ መቀበር እንደሚፈልጉ ለህወሃት ብዙ አማላጅ ልከዋል፡፡ ነገር ግን ያኔ ህወሃት ጠንካራ ነዉ ኦነግን የኦህዴድ ማስፈራሪያ ከማድረግ የዘለለ አይፈልገዉም ነበር፡፡ አሁን ግን የፖለቲካ የበላይነት በኦህዴድ እየተወሰደበት ስለሆነ ምናልባትም የእነ ሌንጮ ፖለቲካ ዉስጥ መሳተፍ ለህወሃት የተወሰነ ሊያግዘዉ ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ የክልል ፓርቲዎች በምርጫ የማሸነፍ እድል አላቸዉ፡፡ ለምሳሌ ኦፌኮ እና አዲስ የሚመሰረተዉ የአማራ ፓርቲ፡፡ እኒህ ፓርቲዎች ከወታደር ቤት፤ ከደህንነቱ፤ ከፖለቲካዉ የተባረሩ እና ሲስተሙን በደንብ የሚያዉቁ አማካሪ ካላደረጉ ወይም አባል ካላደረጉ ቢያሸነፉ እንኳን ፓርላማ ላይ ብቻ ተወስነዉ መቀርታቸዉ ነዉ፡፡ ህወሃት ትግራይ ላይ አንድሺህ አንድ ግዜ ያሸንፋል፡፡ ስለዚህም ባለዉ የወታደር እና የደህንነት የበላይነት እንደገና ስልጣኑን ይቆጣጠራል ማለት ነዉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያሸንፉ የፓርላማ ወንበር ብቻ ሳይሆን የወታደሩንና የደህንነቱን ስልጣኖችም የሚያገኙበት መንገድ አብሮ መሰላት አለበት፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የሚሆነዉ በተወሰነ መልኩ የምርጫ ሂደቱ ክፍት ሊሆን ችላል በሚል ታሳቢነት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ክፍት ባያደርገዉ እንኳን አሁን ያለዉ ወጣት ማስገደዱ አይቀርም ኮሮጆም ላለማስገልበጥ መተናነቁ አይቀርም፡፡