የሰው ሕይወት በተቀጠፈበት የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ የፀጥታ ኃይሎች አላስፈላጊ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
127ኛው የዓድዋ ድልን ለማክበር በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ፣ አስለቃሽ ጭስ፣ የፕላስቲክ እንዲሁም እውነተኛ ጥይቶችን መተኮሳቸውን ኢሰመኮ ዛሬ የካቲት 24/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኢሰመኮ የፀጥታ ኃይሎች ሰጥተውታል ባለው ከልክ ያለፈ ምላሽ በእድሜ ገፋ ያሉ እና ሕፃናትም ጭምር ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጿል።
በዚህም ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት እንደተቀጠፈና፣ በርካቶችም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
በክብረ በዓሉ ወቅት ሕይወቱ የጠፋው ሚሊዮን ወዳጅ በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሲቪክስ መምህር መሆኑን እና በጥይት ተመትቶ መገደሉን የሟች ዘመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባሉ እንደሆነ የገለጸው ሚሊዮን ወዳጅ የዓድዋ በዓል ለማክበር በወጣበት ከመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ተመቶ መገደሉን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥውን የጣሊያን ጦር ድል የነሳችበት ዓመታዊውን የዓድዋ ድል በዓል ለመታደም በምኒልክ አደባባይ በተሰበሰቡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በአስለቃሽ ጭስ እና በቆመጥ መበተናቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ በአደባባዩ አካባቢ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል በርካቶች በአስለቃሽ ጭስ እና በድብደባ ተጎድተው ወደ ሐኪም ቤት መወሰዳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
- የዓድዋ በዓልን በአጼ ምኒልክ አደባባይ ለማክበር የወጡ ታዳሚዎች በአስለቃሽ ጭስ ተበተኑ2 መጋቢት 2023
- በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር የወጣ አንድ መምህር በጥይት መሞቱ ተነገረ3 መጋቢት 2023
- ጉዞ ዓድዋ – የጀግኖችን ዳና የተከተሉ ተጓዦች ታሪክ2 መጋቢት 2023
ኢሰመኮም በዛሬው መግለጫው በምኒልክ አደባባይ የዓድዋ ድል በዓል እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስን ዓመታዊ በዓል እያከበሩ በነበሩ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በኃይል አላስፈላጊ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወስደዋልም ብሏል።
በምኒልክ አደባባይ ዋናው ዝግጅት ላይ ሕዝቡ እንዳይታደም ወደ አደባባዩ የሚወስዱት መንገዶች ተዘግተው እንደነበር እና እንዳይተላለፍም በፀጥታ ኃይሎች ታግዶ እንደነበር ኢሰመኮ ገልጿል።
ይህ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ሕዝቡ በተለምዶ እንደሚያደርገው ምኒልክ አደባባይ እንዲሁም በአቅራቢያው በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዓልን ለማክበር በሰላማዊ መልኩ ተሰባስቦ እንደነበርም ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህ በዓል ላይ ያጋጠመው ክስተት በተመለከተ አብን ባወጣው መግለጫ የፀጥታ ኃይሎች በበዓሉ አክባሪዎች ላይ ፈጽመውታል ከተባለው ድርጊት ጋር በተያያዘ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅና የሁሉንም ሰው ሰብዓዊ መብቶች ማስጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው መሆን እንደነበረበትም ኢሰመኮ አስታውሷል።
ድርጊቱን የፈጸሙ የፀጥታ ኃይል አባላትም ሊጠየቁ እንደሚገባ ያስታወሰው የኢሰመኮ መግለጫው “የሕግ አስከባሪዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ በበቂ ሁኔታ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባል”ብሏል።