“ሳያዩ ያመኑ ያዩትን ቢጠይቁ ኃጢያቱ ምንድነው”

ይድረስ ለክቡር ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ (በታዛቢው ታዘበ)

አስቀድሜ በሀገሬ ባሕልና ደንብ መሰረት እንዴት ከረሙ ፣ እንዴት ሰነበቱ ስል ፣ ልባዊ መልካሙን ስሜቴንና ምኞቴን በተለመደው ባሕላዊ እሴት አጅቤ ነው።

    ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁት በወቅቱ እርስዎ ቴዎድሮስ ጸጋዬን አስመልክቶ በጻፉት ሃሳብ ላይ ሆኖ ሳለ ፤ በወቅቱ ቸኩሎ መልስ መስጠት ነገርን ያባብሳል ብዬ ብእሬን ለማስቀመጥ ተገድጄ ሳለሁ ፤ ሰሞኑን በተደጋጋሚ የርስዎን መሰል ኃሳቦችች ብቅ ብቅ ማለት ስለጀመሩ ፤ በእርስዎ ስም ለሌሎቹም ተመሳሳይ አቋም ላላቸው ሰዎች ቢዘገይም ራሳቸውን እንዲፈትሹ ስል ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ ።

    ለመጀመሪያ ጊዜ እርስዎን ለማወቅ ዕድሉ የተፈጠረልኝ ፤ እዚህ በምኖርበት ዋሺንግቶን ዲሲ ውስጥ በአርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ አስተባባሪነት በሚዘጋጀውጣይቱ የግጥም ምሽት ላይ የዛሬ ፲፭ ዓመት አካባቢ ነበር ። በወቅቱ አንድ አሁን ስሙን ለግዜው የዘነጋሁትን ግለሰብ “ ዕውነት አንተን ወለደ ” የሚለውን የእርስዎን ስነ ግጥም አቅርቦ እስከዛሬም ድረስ በልቤ ተፅፎ እንዲቀመጥ በተፈቀደለት በዚያ ዘመን ተሻጋሪ ልዩ ድንቅ የግጥም ሥራዎ ነው ። ከዛን በኋላም ፤ በተለይ አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የለውጥ ነፋስ መንፈስ በጀመረበት ሰሞን ፤ በወቅቱ አስተዳደሩን ሲገዳደሩት የነበሩትን አንዳንድ አፍራሽ አዝማሚያዎችን በተመለከተ ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሚል ወቅታዊ ስጋትዎን ያካተተ ኃተታ በድሬ ቲዩብ በኩል ቀርቦ በማየቴ ፤ እኔም እንደ እርስዎ ውስጤ ሲረበሸብኝ የነበረውን ስጋት ፤ ያለ አንዳች መቀባባት ፣ ያለአንዳች አድርባይነትና እንደ አንዳንዶች በጎን እጅ ጠምዛዥ እየሰደዱ በአደባባይ እንደ ይሁዳ እየተደፉጫማቸውን በመሳም ፤ እንዲሁም አወቅን እንደሚሉ አድርባይ ምሁራን ጠ/ሚኒስትሩን ከአምላክ የተላኩ ናቸው በማለት ያልሆነ ስዕል ሳይቀቡ “በአሁኑ ጊዜ መጥፎ ዜና ሳይሰማ ፀሐይ ወጥታ እንደማትጠልቅ” ገልጸው ሀገራችን የተደቀነባትን ክፉ ፈተና ዳስሰው ፤ ወቅቱን ተንተርሰው የሰጡትን ልዩ አስተያየትት ስሠማ በእውነት “ኢትዮጵያ” ለክፉ ቀን የሚሆን እርሾ እንዳላት ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም።

በማስከተልም የዶ/ር አብይ አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ላይ ተገኝተው ያሰሙትን ድንቅ ንግግር ሳዳምጥ ነበር ፤ውስጤ እንደ ጭጋግ ጠፍንጎኝ የነበረውን የሀገሬን ሕልውና ጉዳይ ከሥጋት ይልቅ  “የኢትዮጵያዊነት እሴት” ቀለሙ ይደብዝዝ እንጅ ጠፍቶ አይጠፋም የሚል እሳቤ እንድጨብጥ ያስደረጉኝ።

  ይህንንም እንድል ካደረጉኝ ነገሮች ዋነኛው ፤ በተለይ በስነ ምግባር መጉደል ምክንያት የተከሰቱትን ጉድፎቻችንን በሰፊው ተንትኖ ትውልድን ማስተማር፣ ማረም ብሎም የማዳን አካሄድ፣ ያለ አንዳች መሸራረፍ ፣ ይሉኝታ፣ ቦታና ሁኔታን ሳይመርጡ ሙያዊ ግዴታዎን ሚዛናዊና ትምህርታዊ በሆነ መልኩ በድፍረት ማቅረብዎን ሳይ ያ ድሮ በልቤ ተፅፎ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ቀለም ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ ካደረጉ ታላላቅ ኢትዮያዊ ምሑር አንዱ ነዎት ብዬ ፤ በአደባባይ ወጥቶለመመስከር ማንም አይቀድመኝም።

  በቀደም ዕለት ባደረጉት ንግግር መሐል ከጠቀሷቸው የውጭ ምሑር አንዱ የሆኑት “Noam Chomsky” የጠቀሱትን “አሸባሪነትን ከአለማችን ለማጥፋት ካስፈለገ ቀላል ነው። አለመተባበር የሚለውን እንግሊዝኛው  “Everyone’s worried about stopping terrorism. Well, there’s really an easy way: Stop participating in it.” የሚለውን ኀሳብ ተጋርተው እርስዎም አክለው ጓሮህ እንዲበቅል ያልፈለግከውን አለመትከል ነው።” ብለው ነበር ። ስለዚህእንደ እርስዎ አባባል ሰው የማይወደውን እንደማይዘራ ሁሉ የሚፀየፈውንም ቃል አይጠቀምም ማለት ነው። መቼም ይኼንን ለእርስዎ አልነግርዎትም። ብዙ አደባባይ ሲነገሩ ጆሮአችንን ስቅጥጥ የሚያደርጉ ቃላቶች እንዳሉ ሁሉ እንዲሁ አጥንታችንን የሚያኮሰምኑ፣ ያልሆነውን እንደሆንን አድርገው የሚነገሩ ብዙ አባባሎች አሉ ። የኔና የእርስዎ ድርሻ ደግሞ እነዚህ ሳይፈለጉ የበቀሉ አረሞችን መንጥሮ እንደሚጥለው ገበሬ የቃላትና የአባባል አረሞችን ከውስጣችን መንጥረን በመጣል እነዚህን ጸያፍ ቃላሎችን እና አባባሎች ባለማስተጋባት ክፉውን ሀሳብ በመቃወምና አለመተባበር ዋነኛው ተግባራችን ሲሆን ግዴታችንም መሆን አለበት።

   እንግዲህ ለዚህ ፅሑፍ መነሻ የሆነኝን ኃሳብ ያገኘሁት በአንድ ድህረ ገፅ ላይ ከዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ ለርዕዮት ሚዲያ አዘጋጅ ለጋዜጠኛ “ቴዎድሮስ ፀጋዬ “ተፃፈ በተባለው መልዕክት ላይ ነው ። ይህንን መልዕክት ከሌላ ከሶስተኛ አካል ለማጣራት ባለመቻሌ ከርስዎ የተፃፈ ካልሆነ የኔን ፅሑፍ በይቅርታ አልፈው ስምዎን የማጉደፍ ስራን የሚሰሩትን ወጥተው ማውገዝ ይኖርብዎታል።

በእርግጥ ይህ ፅሑፍ የርስዎ ከሆነ ግን ያን ዘወትር በደስታ እንድሰክር ያደርገኝን ግጥም የፃፈ አዕምሮ …ያ በዚህ ተስፋ አስቅራጭና ወጀብ በበዛበት ጊዜ እንደ ነቢዩ ሙሴ ተስፋ ያስጨበጠኝን መልእክት ያፈለቀ ጭንቅላት … ያ በሚሊኒየም አዳራሽ የሞራል ልእልናዬ ከፍ እንዲል ያደረጉትን ድንቅ የህብረተሰቡን የሞራል ዝቅጠት ተንትኖ ያስረዳ ንግግር አስክዶ ከዚህ በፊት የእርስዎ ስራ ያስፈነጠዘኝን ያህል በተቃራኒው ሰውነቴ ኮስምኖ ውስጤ ተሸማቆ የሆነ ነገር ከውስጤ እንዲተን ምክንያትሆኖኛል ስልዎት ሌላ የምገልጽበት ቃላት ተቸግሬ እንደሆነ እንዲረዱኝ እፈልጋለሁ ።

  ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው ። እኔ እርስዎንና ስራዎችዎን በጣም እንዳከብርና እንዳደንቅ ካደረገኝ ነገሮች መሐከል እነዚህ ሁለቱ መሰረተ ኃሳቦች   በተለየ መልኩ አንኳር አንኳር ድርሻዎችን ይወስዳሉ። ይኀውም ፩ኛ ከንግግርዎ የተረዳሁት እንደ ሌሎች ግብዝና ራስ ወዳድ ፤ ባለሥልጣን ፊት ሲደርሱ እንደፋ ፤ እንቀንጠስ እንደሚሉት ወይንም ደግ ደጉን ብቻ እያነሱ እንደሚያሽቃብጡት ራስ ወዳድ ግለሰቦች ሳይሆን ምንም ባልተቀባባና ባልተጋነነ መልኩ ስህተት መስሎ የታየዎትን ጉድፍ በመንቀስ አለምንም ማወላወልና መፍራት መናገርዎ ሲሆን ፤

  ፪ኛው ደግሞ ለዛሬ ፅሑፌ መነሻ የሆነኝ የሀገራችን ዋነኛ ወቅታዊ በሽታ ስለሆነው “የስነ ምግባር” ጉድፈት ወይም ጉድፎቻችን የተናገሩዋቸው ናቸው። እኔም በዚህ መቶ በመቶ በተናገሯቸው እስማማለሁ ። ከርስዎ ንግግር ልጥቀስና  “ነውጡ የበዛው በአጠቃላይ ማኅበረሰባችን ጠንካራ የስነ ምግባር እሴት ስለጎደለው ነው ካሉ በኋላ…” እንድያውም ትንሽ ዝቅ ብለው እንደዚህም ብለው ነበር።  “አጥፊዎችን ከማኅበረሰቡ አደባባይ አቁሞ በስም ጠርቶ ያለመገሰፅ፣ በሕግ ፊት አቁሞ ያለመቅጣት ወንጀልን ያበረታታል፣ ያበራክታል ። ሌሎችም የግፍንና የወንጀልን ፍሬ እንዲመኙ ያደርጋል ባሉትም ከእርስዎ ጋር በሰፊው እስማማለሁ ። ከዚህበፊትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው አባባል ለዶ/ር አብይ በላኩት ግልፅ ደብዳቤ ላይ “ስም ጠርተን እንሸልማለን እንጂ ስምጠርተን፣ ሸንጎ አቁምን አንወቅስም።” ብለው ነበር ። ታዲያ በእነዚህ ከላይ በዘረዘርኳቸው ነገሮች ሁሉ ካመኑ እንዴት ከራስዎ አመለካከትና ፕሪንሲፕል ውጭ የሆነ ነገር ይፈፅማሉ ። በቅርብ ቀን የርዕዮት ሚዲያ አዘጋጁን ቴዎድሮስ ፀጋዬን ልምከርህ በሚል መሪ ቃል በተለቀቀው ደብዳቤዎ ላይ፣ በእኔ አተረጓጎም ምክር ሳይሆን ሲኮንኑት ተስተውለዋል ።

   በቅድሚያ እዚህ ጋር አንድ ነገር መሠረት በረገጠ መልኩ “እንድንገነዘብ” እፈልጋለሁ ። ጥያቄዬ ቴዲ ለምን ተተቸ ፧ ወይንም ቴዲ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም ብሎ ብሎ ለመሞገት ወይም ለቴዎድሮስ ፀጋዬ ጥብቅና ለመቆምና በሱ ስም ለመከራከር አይደለም ። ማንኛውም ኃላፊነት የሚሰማው ግለሰብ ሕብረተሰቡን የሚጎዳ ማንኛውም አይነት አመለካከትም ሆነ አካሄድ ሲመለከት ፤ ኃላፊነት በተላበሰ መንገድ የተሰማውን አስተያየት ጨዋነትን ተንተርሶ ፤ ማሰማት ፣ ማስተላለፍ መናገር እና መገሰጽ የሥነ ምግባር ኃላፊነት ብሎም የዜግነት ግዴታው ያዘዋል ። በተለይ እንደ እርስዎ ስለ “ስነ ምግባር” ጉድለት ያመጣውን ጣጣ በጥልቅ ዘርዝሮ የተቸ ሰው እርሱ ራሱ በተጸየፈው ወጥመድ ተይዞ ሲንደፋደፍ ማየት ግን እጅግ ያሳዝናል ። ልምከርህስ ብሎ የጀመሪ መካሪ አፍራሽ ብሎመንደርደር ምን የሚሉት ምክር ነው የሚወጣው ። ተመካሪ ተብዬውስ ከዚህ አካሄድ ምንድነው የሚያተርፈው ፧ መቼም እንደ እርስዎ በአስተማሪነት ያለፈ አንጋፋ ምሁር ይሄን ያጣዋል ብዬ አልገምትም ። ማስተማር፣ መምከር፣ መገሰፅ አልፎ ተርፎም ተመካሪው ካልሰማ ከላይ እንደጠቀስኩት በአደባባይ ወጥቶ መገሰፅ ተገቢ መሆኑን ባልክድም ፤ እርስዎ የተጓዙበት መንገድ ግን ግለሰብን የማንኳሰስ ፣ የመኮነንና መብትን የመጋፋት አባዜ የተጠናወተው ይመስላል ።

ቴዲ ለምን ተተቸ ፧ ቴዲ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም ፤ ሐቁስ ማን ጋር ነው ያለው ፤ ማስረጃውስ ትክክል ነው አይደለም ወዘተ ፣ወዘተ ፣የሚለውን ለማብራራትምሆነ ለማፍታታት አልባዝንም ፤ ምክንያቱም ቴዲ እራሱ በተወቀሰበት ርእስ ፣ “እኔ ክስ እለዋለሁ” በተከሰሰበት ጉዳይ ወይም መጠይቅ ላይ ራሱ ቴዲ መልስ መስጠት የሚችል በመሆኑ ነው ። ከዛም በላይ የቴዎድሮስን ዝግጅት ያደመጠው ሕዝብ ነገሮችን በራሱ ህሊና አመዛዝኖ ሚዛናዊውን ፍርድ ይሰጣል ብዬ ስለምገምትም ነው።

  እኔን ያሳዘነኝና እንቅልፍ የነሳኝ እነዚህ ሁለት ነገሮች ናቸው ። እነሱም አንደኛ ቴዎድሮስን ከዘውግ ጋር ለማዛመድ የተሞከረው አካሔድ ነው። እውነት እውነት እልዎታለሁ እንደ እርስዎ ያለ ትልቅ የስነ ፅሑፍ አዋቂና ለሀገር ተቆርቋሪ ከሆነ ግለሰብ ፤ የማይጠበቅ የሰሞኑን የወረረሽ አባዜ ተጋርተው እንደሌሎቹ የዘር ሐረግና ግንድ እየጠቀሱ ደም ማቃባቱን ሲፈፅሙ ሳይ ኃዘን ብቻ ሳይሆን በሽታም እያዛመቱ መሆኑን ስገልጽልዎት ከከባድ ሀዘን ጋር ነው ። የተጠቀሙትን ቃል ልግለጽና

“በተለይ የሕወሀት ፈላጭ ቆራጭነት ማብቃት የማመዛዘን አቅምህን ተፈታትኖታል።”ሲሉ ተደምጠዋል ። ለኔ መቼም አንድ “የማይፈልገውን ፍሬ ከጓሮው አይዘራም።” ብሎ ካስተማረኝ አስተማሪ ፤ እንዲሁም በሽብርተኝነት ላይ የጠቀሱትን አባባል ማለትም የማትወደውን አካሄድ አትተባበር ብሎ ጭብጥ ካስያዘኝ ምሁር ፤ እርሱ ራሱ ዘመን ባነገሰው የጎሳ ወረርሺኝ በሽታ ተለክፎ ፤ሰውን በዘር ሐረግና ግንድ ለመፈረጅ የተጓዙት ጉዞ በጣም አስነዋሪ፣ አሳዛኝ፣ አስከፊና አስጸያፊ መንገድ መሆኑን የቱ ጋር እንደሳቱት ለማመን ግራ የሚያጋባ ነው ። በአንድ ወቅት ጊዜው በመርዘሙ በትክክል ባላስታውሰውም ከብዙ ውዝግብና ጭቅጭቅ በኋላመላው የአማራ ድርጅት መመስረቱን አስመልክቶ በወቅቱ ይታተም የነበረው የጦቢያ መጽሔት እንዲህ የሚል ቃል ይዞ ወጥቶ ነበር ፤  “የወቅቱ የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቅ በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመሩ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የእንኳን ደስ አለህ የእቅፍ አበባ ላኩላቸው ብሎ ነበር።” እንግዲህ ምንለማለት እንደፈለኩ ሳይገነዘቡት አይቀርም ። እርስዎ በግልዎ አተያይ ይህንን መንገድ ቴዲ ተከትሏል ብለው ቢያምኑ እንኳን ፣ በተለይ በቅርብ ለሚያውቁትናላስተማሩት ቀርቶ ለማያውቁትም ሰው ቢሆን እንኳን  በግል ሃሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ ምክርዎን ሊለግሱት በተገባ ነበር እንጂ ይዘውት አደባባይ መውጣትዎ ምን ያህል አዕምሮዎ በመጥፎ ወረርሺኝ የዘውግ አካሄድ የተሞላ መሆኑን ያሳያል ። ለእኔና መሰሎቼ ስሕተት ሰርተዋል ብለን እናምናለን ። ነገሮችን እየለቀሙና እየነቀሱ ቢደረደሩት ጥቅም የለውምና ለማስረጃ ያሕል ይህንን ካልኩ ወደ ሁለተኛው ክፍል ልለፍ።

  ራስዎ በአስረጅነት ከጠቀሱት ከ Noam Chomsky ቃል ልዋስና ወደ ጥያቄዬ አልፋለሁ። Noam Chomsky እንዲህ ይላል።  If we do not believe in freedom of expression for people we despise, we do not believe in it at all.  ይላል ። ዲስፓይስ የሚለውን ቃል ብዙ ትርጉም ቢኖረውም ከራሴ ጋር ሙግት ገጥሜበት ለዚህ አባባል የኔ ቃል አፈታት ነው “መጥላት” የሚለው ቃል ለአባባሉ ይቀርባል ብዬ ስላመንኩ በዚሁ ቃል ልጠቀምና የትርጉሙን ይዘት እንየው ። “የሚጠሉትን ሰው በነፃነት ሀሳቡን የመግለፅ መብቱን ካላመኑበት በአጠቃላይ በነፃነት ኃሣብን መግለፅን አያምኑበትም ማለት ነው” ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል ። እንግዲህ በራስዎ አንደበት የገለፁት አስተምሮውን በማስረጃ መልክ የሚጠቅሱት ሰው እንኳን ከርስዎ ኃሳብ ጋር ይጋጫልማለት ነው ። ቴዲ በነፃነት ኃሳቡን የመግለፅ መብቱን ሊጠብቁለት ይገባል ።   ምናልባት በቀላል አገላለፅ ለርስዎ ባይመችዎት፣ ባይጥምዎት፣ ባይስማማዎት አባባሉን አልቀበለውም ማለት ይችላሉ ። ይኼ ማለት ግን እርስዎ ብቻ ትክክል ነዎት ማለት አይደለም ወይም በተቃራኒው ቴዲ ትክክል ነው ማለት አይደለም። እንደ አንድ ሀገሩን እንደሚወድ ጠንቃቃ ምሑር ዜጋ፣ ቴዲ ያቀረባቸውን መከራከሪያ ኃሳቦች አንድ በአንድ እየነቀሱ፣ ማስረጃ እያጣቀሱ ኃሳቡን በኃሳብ ማሸነፍ ሲቻል ግብረገብ  በጎደለውና በማንኳሰስ ካንድ ምሁር የማይጠበቅ አባባል ተጠቅመዋል ። እጠቅሰዋለሁ ፣ “የ እናትህን ጡት ለመንከስ ምን ያህል ለመሔድ እንደተዘጋጀህ አስቤ አዘንኩ ።” ብለዋል ። እውነት ቴዲ ከዘመነ ዘውገኞቹ ቃል በቃል በትርጉም ሳይሆን በአደባባይ በግልጽ  ለኞ የማትሆን “ኢትዮጵይ” ብትንትኗ ይውጣ ብሎ የሰበከውን ሰው ለመናገር ሳይደፍሩ ቴዎድሮስ ላይ እንደዚህ ያለ መራር ቃል ሲያወጡ ሳይ እጅግ ተደናግጫለሁ ። ይገርምዎታል በዚህ አባባልም ከእርስዎ መቶ እጥፍ የበለጠ አድናቂዎችና አክባሪዎችዎ እጅግ አዝነናል ደንግጠናል ። ልብ ይበሉ ፦ ኃሳብዎን በነፃነት መግለፅ መብትዎን እየተጋፋን ወይንም እየነፈግን አይደለም ። የተከተሉት ሰውን የማንኳሰስና የማቀጨም መንገድ አግባብ አይደለም አልን እንጂ ። ለመሆኑ የእርስዎ አስተሳሰብ ትክክል የቴዲ አስተሳሰብ ደግሞ አፍራሽ የሆነበት ምክንያት ማስረጃዎ ምንድነው ፧ በ፲፱፮፮ ዓ/ም የፈነዳውን የሕዝብ አብዮት መቀልበስ አንስተዋል። ይገርምዎታል የዛን ጊዜ ከወዲሁ አስተዳደሩን ማስረጃ እየጠቀሱ ቢተቹትና ቢገዳደሩት ኖሮ ምናልባትም “ኢትዮጵያ” ዛሬ ያላት ቅርፅ ባልኖራትም ነበር። “ቪቫ መንግሥቱ” ፣ “ከቆራጡ መሪ ጋር ወደፊት” ፣ “አብዮት ልጅቿን ትበላለች” ፣ “ፈጣን ነው ባቡሩ” እየተባለ ባዶ ጩኸት ከማሰማበት ባሻገር በእርግጥ እንደ ዘመኑ ሚዲያ በቀላሉ ሰው ጋር መድረስ ቀላል አልነበረም ። መንግሥትን በጊዜ ማረም ባለመቻላችን አሁን ያለንበት  ጣጣ ውስጥ ገብተናል ። በደርግም ሆነ በአሁኑ አስተዳደር እስካሁን የተቸርነው ነገር ቢኖር ባዶ የቃላት ጋጋታ ነው ። በቃላትና በስብከት ደግሞ የተገነባም ሀገር ፣ የፈረሰም ችግር የለም ። ተግባር ሲታከልበት እንጂ ። ምናልባት ቴዲ የተናገረውን ጠቅሰው ኃሳቡን መሟገት ባይችሉም እንኳ በወንድማዊ ፍቅር ችግሩን እንደሚረዱት ተገንዝበው ያከረረውን የትችት ዱላ እንዲያላላው ሊመከሩት በተገባ ነበር።

    ቴዲ ያደረገው እርስዎ በንግግርዎ የጠቀሱትን ነው። ከርስዎ ቃል ልድገመውና እንዲህ የሚል ሐረግ ይነበባል። “ አጥፊውችን ከማህበረሰብ በአደባባይ አቁሞ በስም ጠርቶ ያለመገሰፅ ወንጀለኛን እንደሚያበረታታ ገልፀው ፤ በተቃራኒው ቴዲ የወቅቱን የሀገሪቱን ርዕሰ ብሔር እሱ በተረዳው መንገድ የተናገሩትንና የሚሰሩትን አመሳክሮ ስህተት መስሎ የተሰማውን አደባባይ ወጥቶ መናገሩ ኃጢያቱ የቱ ላይ ነው ፧ ዕውነታውን መሞገጽ ሲያቅትዎት ቴዲ ድሮ ስለ አበባና ቢራቢሮ ትፅፍ ነበር አሁን እንዴት ወደ መንግስት መተቸት መጣህ በማለት ቅኔ አዘል ንግግርዎን ሰንዝረዋል ።

  ለዚህም ሰዎች የፈለጉትን ኃሳብ በነፃ የማንሸራሸር ኃሳባቸውን እየተጋፉ ነዎት ልልዎት ደፈርኩ ፤ለቴዲ ከማደንቅለት የገጣሚነት ችሎታው ባሻገር ነገሮችን አስቀድሞ የማየትና ያመነበትን ነገር ያለ አንዳች ፍራቻ መግለጽና የራሱን እይታ በሰፊው ተንትኖ የማስረዳት ክህሎቱ ድንቅ ነው ፤ ስለዚህም ከስነ ፅሁፉ ጎን ለጎንለሁላችንም ሕመም የለቀቀብንን የሀገራችንን ሁኔታ መከታተሉንም ሆነ የእሱን እይታ ማጋራቱን አደንቅለታለሁ፤ በዛ ላይ ከላይ እንደጠቀስኩልዎ አቋም የለሽ አድርባይ ሁሉ እየተደፉ ጫማ ከመሳም ባሻገር ሃሳባቸው ወንዝ እንደማይሻገር ገብቷቸው ፤ ያልተቀበላቸውን ህዝብ በጠመንጃና በቆንጨራ ከማስፈራራት ይልቅ ችግር የመሰላቸውን አካሄድ ነቅሰው በኃሳብ መሞገትን የመሰለ ጤናማ አካሄድ ሊለመድና ሊበረታታ ይገባዋል እንጂ ሊወቀስበት አይገባም … እንግዲህ እርስዎም “ምክር” ብለው በጠሩት ምክር መሰል ኩነናዎ ፣ ምክንያቱም በኔ አረዳድ ምክር ሳይሆን ክስ መሰል ኩነና ነውና ያካሄዱት ፤ የትም እንደማያደርስዎ ልገልጽልዎ እወዳለሁ ። ከዚህ በፊት የመንግሥት ባለስልጣናትን ሳይሆን ስም አልጠቅስም … እነ እከሌን  ጠርተህ ትዘረጥጥ ነበር ብለዋል ። ሲጀመር መዘርጠጥ የሚለውን ቃልለምን መረጡ። እኛም ቴዲጋ የቀረቡት ጎምቱ የተባሉ ምሑር የተጠየቁትን በማስረጃ ማስደገፍ ስላልቻሉ ከቴዲ ወቀሳ አላመለጡም ። መቼም ይሄ ትክክለኛ የጋዜጠኛ አካሄድ ይመስለኛል ። በእርስዎ  አመለካከት አንድ ትውልዱን እውነቱን ሳይሆን “ተረት ተረት” እያፃፈ ወደ አላስፈላጊ አመለካከት ለመቀየር የሞከረን ሰው መሞገት ስህተት ነው ብለው ካሰቡ በድጋሚ ራስዎን ይመርምሩት እላለሁ።

  አንድ ሰው የሚከበረው በስራው ነው እንጂ በእድሜው አይደለም። በዕድሜ የሚገባውን ክብር ማንም ይለግሰዋል የሞራል ግዴታ ያዛልና ። በሙያ ውስጥ የሚገኝ ክብርን የሚፈልግ ግለሰብ ግን ሙያዊ ግዴታውን በብቃት መወጣት ይጠበቅበታል። በስተ መጨረሻም ሌላው ያሳዘነኝ አድሎአዊ አካሔድዎ ነው ። ለምሳሌቴዎድሮስ ከዚህ ቀደም የሌላ ፓርቲ ደጋፊ ነው እንበል። “እንበል” ነው ያልኩት ። በደንብ ይህችን አሳምረው ይያዙልኝ። እንበልና ነው የምለው ፤ሌሎቹ ባልታደሰው ኢህአዴግ ውስጥ ባለ ስልጣን የነበሩ ሰዎችን እናስታውስ ፤ (ያው አሁንም ያለው ኢህአዴግ ነው ታድሻለሁ ከማለቱ በስተቀር)። ደጋፊ አይደለም ያልኩት። ባልታደሰው ኢህአዴግ ውስጥ ባለሥልጣን ሆነው፣ ባለፍንበት ፳፯ የመከራና የሰቆቃ ዘመን አብረው ሲያስሩና ሲያሳስሩን የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ድንገት ተነስተው የሔድንበት መንገድ አስከፊ ነበር፣ ተሳስተናል፣ አጥፍተናል ፤ ሕዝቡ ይቅርታ ከሰጠን ወደፊት ሀገራችንን በአንድ ሆነን እንገነባለን፤ ሲሉ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ መልኩ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ነፍሱን እስከመስጠት ድረስ አጨብጭቦና አልቅሶ ድጋፉን አሳይቷል። እንግዲህ እነዚህ  ከሥርዓቱ ጋር እጅና ጓንት የነበሩ ሰዎች ፣ዛሬ ተቀይረናል ብለው ኢትዮጵያዊነትን ሲሰብኩ በደስታ እየተቀበልናቸው ቴዎድሮስ ተነስቶ ኢትዮጵያዊነትን ቢሰብክ ለምንድነው ውሸትህን ነው የምንለው፧ እንዲህስ ለመገመትና ለመናገር ያስድፈረዎ ምንድነው ፧ መቼም ከፈጣሪ በቀር የሰውን ልብሊፈትሽ የሚችል ብቃት ያለው ፍጡር ካለ ይንገሩን ። እኔ እውነት እውነት እልዎታለሁ “እኔ የምደግፈውን ካልደገፍክ ጠላቴ ነህ አካሔድ ፤ እኔ ብቻ ነኝ ትክክልማለት የት እንዳደረሰን ለርስዎ መንገር ለቀባሪ አረዱት ይሆንብኛል። ለዚህም ነው በርዕሴ ላይ   “ ሳያዩ ያመኑ ያዩትን ቢጠይቁት ኃጢያቱ የቱጋ ነው “ ያልኩት።

  እንደው ራስዎ ሲያስቡት ስንትና ስንት በሚዲያና በአደባባይ ወጥተው ሕዝብና ሕዝብ ለማፋጀት ሌት ተቀን የሚጥሩትን ሰዎች አጥተዋቸው ነው እንዲህ አይነት ፈሩን የለቀቀ ትችት ቴውድሮስ ላይ ለማቅረብ የደፈሩት፧ እኔን አይመስለኝም። ደግሞስ በዚህ በነጮች ሀገር “whistleblowers” የሚባል ነገር እንዳለአያውቁም ለማለት አልደፍርም ። “whistleblowers” እንዳሉ ሁሉ “whistleblowers protection act” የሚባልም ሕግ አለ። ይህ ህግ በማንኛውም በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚፈፀምን ሕግን የጣሰ አካሔድ የሚያጋልጡ ሰዎችን የሚጠብቅ ሕግ እንደሆነ የሚጠፋዎት አይመስለኝም ፤ የነዚህግለሰቦች ተግባር በመንግስትም ሆነ በማንኛውም መንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ህግን ያልተከተሉና ህግን የጣሱ አካሄዶችን ሲያስተውሉ ለሚዲያ ማጋለጥና እርምት እንዲወሰድ ማስገንዘብ ነው ። መንግስትም ይህንን በተመለከተ አዋጅ አርቅቆ እነዚህን ግለሰቦች የመንግስት ከለላ እየሰጠ ጥበቃ ያደርግላቸዋል ። መቸም የሥራአቱ ቁንጮዎች ለምን ይተቻሉ፧ እንደማይሉ ዕምነቴ ነው። አሁን በማስተዳደር ላይ ያሉት ሰዎች ተስፋ ስለመገቡን ብቻ ያለውን ሰቆቃ ችለን አጨብጭብናል፣ ዘፍነናል፣ ሞተናል፣ ጮኸናል ። ታዲያ እንደኛ ተስፋን መሰነቅ ያልቻሉ ቅሬታቸውን ቢያሰሙ ለምን ከዚያ በሚፀየፉት የብሔር ወረርሺኝ ፈረጁዋቸው፧ መቼም በቅርቡ አስተያየትዎን እንደሚያሰሙን ተስፋ አደርጋለሁ፥

   በመጨረሻ በዚህ ቃል ልሰናበትዎ

በመፅሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፰ ከቁጥር ፲፱ ፥ ፳፫ ላይ እየሱስን ለሊቀ ካህኑ ያልተገባ መልስ ሰጥተኃል ብሎ ከሎሌዎቹ አንደኛው በጥፊ እንደመታው ያትትና፤ኢየሱስ የመለሰለትን መልስ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል ።

“ኢየሱስም መልሶ ክፉ ተናግሬ እንደሆንሁ ስለ ክፉ መስክር መልካምም ተናግሬ እንደሆነ (እንደዛው) ግን ስለምን ትመታኛለህ አለው።”

ቴዎድርስም ዋሽቶ እንደሆነ ዋሽተሀል፣ ያልገባው ነገር ካለም ማስተማር፣ ካልደገፉትም መቃወም ሲቻል ኃሳቡን ትቶ ግለሰቡን ከዘር ግንድ ጋር ማዛመዱ በምድርም በሰማይም አስፀያፊ ነውና ያርሙት እላለሁ

አክባሪዎ  ታዛቢው ታዘበ

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም።

(ማስታወሻ፣ ጽሁፉ የጸኃፊው ምልከታ እንጅ የኢትዮታይምስ ሚዲያ አቋም አይደለም)