የዶ/ር አቢይ ለውጥ የትግራይን ሕዝብ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ስለዚህ እንደግፈዋለን!

(በክብሮም አድሐኖም ገብረየሱስ)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የትግራይን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ግን የማይወክሉ ግለሰቦች በፌስበክ አካውንታቸው ዶ/ር አቢይ አሕመድ በፓርላማ የተናገሩትን በማጣመምና ነገር በመሰንጠቅ የትግራይ ሕዝብ ጠላት አስመስለው እየወነጀሉ ይገኛሉ። ይህንን ዝም ማለት ይቻል ነበር ግን ነገሮች በየጊዜው እነዚህ ህዝብን የሚያሸብሩ ወሬዎች እየተባባሱ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ እስካሁን ድረስ እያደረጉ ያሉት ተግባር የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ ነው ወይስ የሚጠቅም? የሚለውን ነጥብ በነጥብ ተዘርዝሮ ሐቁ ሊገለፅ ይገባልና ዝርዝሩ እነሆ፦

1ኛ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ፈለገው የኢትዮጵያ ክልል ተዘዋውሮ መስራት መኖር እንደሚችል ነው የሰበኩት ይህ የትግራይን ሕዝብ ይጎዳል ወይስ አይጎዳም? እስኪ አንይ ልክ እንደሚታወቀው አብዛኛው ትግራዋይ ከዝቅተኛው ከልዋጭ ልዋጭ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ባለሐብት የሚታወቀው ከክልሉ ወጥቶ ሲለፋ ሲደክም ነው። የሚታወቀው በታታሪነቱ እና ስራ ባለመናቁ ነው። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንም ሰው በፈለገው ክልል ተዘዋውሮ ሰርቶ መብላት በነፃነት ሊኖር ይገባዋል ብለው ማለታቸው ከማንም ብሔር በላይ ከክልሉ ወጥቶ እንደ ጨው ተበትኖ የሚታትረውን ሐቀኛ ትግራዋይን በነፃነት ተዘዋውሮ ሐብት እንዲያፈራ እንዲበለፅግ ያደርገዋልና የትግራዋይ ጠላት የሚሆኑት በምን ሂሳብና ስሌት ነው።

2ኛ. እነዚህ ነገር ሰንጣቂ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንቃወማቸዋለን ብለው ከተነሱባቸው የሰሞኑን ነገሮች አንዱ ” የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን ነጣጥላችሁ እዩ ሕወሐት ባጠፋው የትግራይ ሕዝብ ሊሰደብ ንብረቱ ሊወድም ሕይወቱን ሊያጣ አይገባውም እውነተኛ የትግራይን ሕዝብ ኑሮ ማየት ከፈለጋችሁ ገጠር ሔዳችሁ እዩ” ማለቱ ነው። ይሄ አሁን ሐቅና ሊያስመሰግን ይገባል እንጂ ምኑ ነው የሚያሰድበው? ትናንት ትናንት ወዲያ እኮ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሐት ጋር በመቀላቀል ሰፊ የጥላቻ ዘመቻ ላለፉት 12 ዓመታት እስከ ዛሬ ድረስ ባላጠፋው ባላደረገው በጭፍን የጥላቻ ፓለቲካ አራማጆች ሲካሔድ ነበር። በዚህ የተነሳ ይህንን ስርዓት ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ በዚህ በተሰበከው የጥላቻ ስብከት ሕወሐት አጥፍቶታል ባሉት በማያውቁት በዘራቸው ምክንያት ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ካጡትና በከፍተኛ ሁኔታ ስጋት ውስጥ ከወደቁት ብሔሮች መካከል የትግራይ ተወላጆች አንዱ ናቸው። ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን ለይታችሁ እዩ ሕወሐት ባጠፋው የትግራይ ተወላጆችን አትጉዱ እውነተኛ የትግራዮች ኑሮ ገጠር ሔዳችሁ እዩ ማለታቸው በተለይም ላለፉት 12 ዓመታት የተረጨውን መርዝ አመከኑ እንጂ ምን አጠፉ? እኝህ ሰው ምንም በማያውቀው ንጹሑን ድሐውን የትግራይ ብሔር ተወላጅ ከተረጨበት መርዝና ከተመዘዘበት የበቀል ሰይፍ ነቢይ ሆነው ሊያድኑት ከመጡት ብሔር በዋነኛነት ትግራዋይን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እናም የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን አትነጣጥሉ የምትሉ ወገኖች የምንላችሁ ነገር ቢኖር ፓርቲና ሕዝብን ለዩ ነው። ከምትከተለው ፓሊሲና የብሔር ፓለቲካ አደረጃጀት የተነሳ ሕወሐት አባሎቿ በሙሉ ትግራዋዮች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ ሁሉም ትግራዋይ የሕወሐት አባልና ደጋፊ ሊሆን አይችልም። ነወሸ ካልን ሕወሐትን በፅኑ የሚቃወሙትን አረናዎችን እና እነ ዶ/ር ሐይሉ አርአያ የመሳሰሉትን ምን ልንል ነው? ስለዚህ ሕወሐት ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቱን በተለየ መልኩ በዋነኛነት እንደ ገዥ ፓርቲ ሲመራ ያለማው ልማት እንዳለ ሁሉ ያጠፋው ጥፋትም እንዳለ ሊታወቅ ይገባልና ሕወሐት ባጠፋው ምስኪኑና ጥሮ ግሮ ላቡን አንጠፍጥፎ የሚበላው ትግራዋይ ሊወቀስ አይገባውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ያስቀመጡት ይህንን ሐቅ ነውና ነገር እየሰነጠቃችሁ የትግራይን ሕዝብ ለማጣላት አትሞክሩ ይሄ ነገር እያጣመሙ የትግራይን ሕዝብ ማስደንበር ጊዜው ያለፈበት ፉሽን ነውና አቁሙ።

ሌላው በጣም የሚገርመኝ የትግራይ ሕዝብንና ሕወሐትን አንድ አድርጎ የሚወነጅል ሲመጣ እነዚህ ወገኖች ዘለው ይሄው አንድ ናቸው አሉ ሊያጠፉህ ነው ይሉታል። ቆይቶ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ሕወሐት አንድ አይደሉም ሕወሐት ባጠፋው የትግራይ ሕዝብ ሊወቀስ አይገባም ሲባሉ ደግሞ ማሊያ ይቀይሩና ይህቺ ሴራ ሕወሐትንና የትግራይ ሕዝብን ልትነጣጥል የመጣች ነች ብለው ይጮሐሉ። እነርሱ አላማቸው አንዳንዶቹ ባለማወቅ ብሔርተኝነትን ከማክረር በቀናነት የጠቀሙት መስሏቸው የሚቃወሙ ሲሆን ሌሎቹ ግን በድሎትና በምቾት እንዲኖሩ ሲባል ምስኪኑንና ደሐውን የትግራይ ሕዝብን ስጋት ውስጥ እየጣሉ በእርሱ ቁማር እየተጫወቱ ከወንድሞቹ ከሌላው ብሔር ጋር በሰላም እንዳይኖር ማድረግ ነው።

3ኛ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ አየሰሩ ካሉት ዋነኛ ስራዎች መካከል ቂም በቀልን ማጥፋትና ይቅርታና ምህረትን ፍቅርን መስበክ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነትና የመባላት የመጠፋፋት ታሪክ የሚበዛበት እንደመሆኑና መልካም መልካሙን ታሪካችንን በማጉላት ይህን የመጠበላላትና የቂም በቀል ታሪክ የሚዘጋ መሪ እየተመኘን ባለንበት ጊዜና ከአሁን አሁን እንደ ሶሪያና የመን ሆንን ስንል ዶክተር አቢይ ፍቅርን ይቅርታን አንድነትን የሚሰብኩ መሪ ሆነው መምጣታቸው ደግሞ “አገኘሁሽ እንደተመኘሁሽ” አንደሚባለው በብዙዎቹ ኢትዮጵያውያኖች ልብ አነዲነግሱ አድርጓቸዋል። ታዲያ ፍቅርና ይቅርታን እርቅን ከሰይጣን ዲያብሎስ በቀር ማን ይጠላልና ነው የሚጠሉት፤

4ኛ. ስንደመር በሚል አባባላቸው የሚታወቁት ዶ/ር አቢይ ቀድሞም ቢሆን ለዘመናት በኢትዮጵያ አንድነትና የመደመር ታሪክ ጉልህ ሚና ያለውና የኢትዮጵያ ሞተር ሲሉ የገለጹት የትግራይ ሕዝብ ከወንድሞቹ አማራዎች፤ ኦሮሞዎች፤ አፋሮች ወዘተ ቢደመር ከማንም በላይ የሚጠቅመው ለእርሱ ነው። አልደመርም ብላ የሄደችው ኤርትራ አለመደመሯ ዋጋ አስከፈላት እንጂ ለኤርትራ አልጠቀማትም።

5ኛ. በመጨረሻም በዓለም የለውጥ አብዮት እንቅስቃሴ ወቅት ብዙዎቹ መሪ ፓርቲዎች ሲፈራርሱ አይተናል። በቅርቡ እንኳን የጋዳፊን እና የየመኑን አሊ ሳልህ የሆኑትን እናውቃለን። ነገር ግን የለውጡ እንቅስቃሴ ፓርቲዎቹን ብቻ ቢያፈርስ ያለና የነበረ በመሆኑ ጥሩ ነበር። ነገር ግን አሳዛኝ በሆነ መልኩ ያፈራረሰው አገርን ነው የሞቱት ንጹሐን ናቸው። ወደ እኛ ሐገር ስንመጣ ግን እኛ ኢትዮጵያውያኖች እና ኢሕአዴግም ጭምር እድለኞች ነን። የለውጥ እንቅስቃሴውን ተከትሎ ሕዝቡን ያወቁና ዘመኑን የዋጁ ከኢሕአዴግ የወጡ አመራሮች ሕዝብ የሚፈልገውን በመገንዘብ በኢሕአዴግ ውስጥ ትግል በማድረግና ጎልተው በመውጣት ሐገሪቷ ከመፈራረስና ከመበታተን አደጋ ወደ አንድነትና ሰላም በማምጣት ፍቅርና ይቅርታን በመስበክ እንዲሁም ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ ሐገሪቱ ወደ ትክክለኛ ሐዲድ እንድትገባ እየተጉ ይገኛሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም በዋነኛነት ኢሕአዴግ እንዲፈጠር ሚናውን የተጫወቱ ሕወሐቶች ለውጡ ከራሳቸው ካሳደጓቸው ልጆቻቸው ከወጣት አመራሮች መምጣቱና መመራቱ ደስ ሊላቸውና ሊደግፉ ይገባቸዋል እንጂ ተቃርነው ሊቆሙ አይገባም።

እንዲሁም እየተደረገ ያለውን ለውጥ ተከትሎ የትግራይን ሕዝብ ጠላት መጣብህ ሊበላህ ነው እያላችሁ ጊዜ ያለፈበት ዲስኩር የምትፅፉና የምትቀሰቅሱ እባካችሁ ልብ ግዙ የትግራይ ህዝብ የሚታወቀው ለውጥ ሲመጣ በማገዝና ለለውጡ ግንባር ቀደም ተሰላፊ በመሆን እንጂ በመቃረን አይደለም። እንይ ከተባለ እነ ዶክተር አቢይ ዛሬ ላመጡት ለውጥ መሰረቱ የትግራይ ሕዝብ ውጤት መሆኑን ነው። ራሱ መሰረት የሆነውንና በደም በመስዋእትነት የተገኘውን የዛሬ የልጆቹን የእነ ዶክተር አቢይ ውጤት ደግሞ ሊያጣጥመው እንጂ ሊበትነው አይችልም አይገባምም። የዛሬ የትግራይ ሰማእታትን በዓል ስታከብሩም አሁን ያለንበትን ውጤትና የደረስንበትን ደረጃ እያጣጣምን እና ሰማእታቱን ክብር በመስጠት ሲሆን ደስ ይላል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
አሁንም ስንደመር እናምራለን እንጠነክራለን ስንለያይ ስንበታተን እንጠፋለን እንበል፡፡
ማሳሰቢያ፦ እባክዎትን ሳያነቡ comment እንዳይሰጡ ይመከራሉ። ሲሰጡም ጨዋ ይሁኑ።