የቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ብዙ እንድምታ ያለው ነው

(በያሬድ ሀይለማርያም) ከ1997ቱ የቅንጅት ሰልፍ ለየት የሚለው በተሳታዊዎች ስብጥር አይነት ይመስለኛል። በነገው ሰልፍ ሦስት አይነት የማህበረሰቡ ክፍሎች የሰልፉ ታዳሚ ይሆናሉ። የመጀመሪያው በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ እና የኢህአዴግ አባል የሆኑ ሚሊዮኖች፤ ሁለተኛዎቹ ኢህአዴግን አጥብቀው የሚቃወሙ እና በቅንጅት ሰልፍም ተሳታፊ የነበሩ ብዙ ሚሊዮኖች እና ሦስተኞቹ በቅንጅት ግዜ ከመንግስት ሊደርስብን ይችላል ያሉትን ጥቃት ፈርተው ጎመን በጤና በማለት ሰልፉን እቤታቸው ሆነው በቲቪ ያዩና ዳር ተመልካች የነበሩ እጅግ ብዙ ብዙ ሚሊዮኖች።

ስለዚህ ይህ ሰልፍ ባጭሩ የሁሉም ሰው እና አቃፊ ነው። በዚህ ሰልፍ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሚገለል የህብረተሰብ ክፍል አይኖርም። ይህ ከሆነ ሰልፉ በቅንጅት ጊዜ ከታየው ታላቅ ሰልፍ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ እጥፍ የሚያስከነዳ ነው የሚሆነው።

ይህ ክስተት ለአገሪቱ ፖለቲካ አዲስ ምዕራፍን ይከፍታል ብዮ አምናለሁ። በአንድ ወገን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ጾታ እና የፖለቲካ አመለካከቶች ግንብ ሆነው ሳይከልሏቸው በጋራ የሚቆሙበት አገራዊ መድረክ መሆኑ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ዜጎች ሳይሸማቀቁና ሳይፈሩ ደስታቸውን እና ስሜታቸውን ሊገልጹ ወደ አደባባይ መውጣት መቻላቸው የሚፈጥረው የመነቃቃት ስሜት ነው።

እንደ እኔ ሰልፉ ዶ/ር አብይን እና ቡድናቸውን ከማወደስ እና ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ ለራሳችንም ቃል ኪዳን የምንገባበት ቢሆን ጥሩ ነው። የሰልፉ ዋና መልዕክትም ከዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች ቢያካትቱ መልካም ነው።

1. ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከውስጡ የዘር ጥላቻን አውጥቶ ሌላኛውን ወገኑን ልክ እንደራሱ ወንድም እና እህት እንዲቆጥር እና ከእንግዲህ ወዲህ ግጭቶቻችንም ሆነ መደመራችን በዘር፣ በኃይማኖት እና በሌሎች የማንነት መገለጫዎች ላይ የተመሰረቱ እና አግላይነትን መነሻ ያደረጉ እንዳንሆን እና ዘረኝነት መርዝ ስለሆነ ከውስጣችን እንዲወጣ ቃል የሚገባበት፤

2. ሁሉም ሰብአዊ መብቶች ለሁሉም በሚል መርህ ሁላችንም የራሳችንን መብት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወገኖቻችንም መብት ዘብ የምንቆም መሆኑን ቃል የምንገባበት፤

3. ከንግዲህ ወዲያ አንባገነናዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ዳግም እንዳያቆጠቁጥና ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት የምንገልጽበት እና በያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ ያለችውን የፈላጭ ቆራጭነት ስሜት አውጥተን ለመቅበር ቃል ኪዳን የምንገባበት ይሁን።

ሰልፉ በተሳካ ሁኔታ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ለአዘጋጆቹ እና ለተሳታፊዎች ምኞቴን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ።

መጪው ዘመን የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብቶች እና የእኩልነት መሰረት የሚጣልበት ይሁን።