(በውብሸት ሙላት) እስከ 2003/4 ዓ.ም. (በትክክል ባላስታውሰውም) ድረስ ዋና ተልእኮው ግጭት መፍጠር የሚመስል ተግባር ውስጥ የተሰማራ አንድ ኮሌኔል(ስሙን ላለመጥቀስ ነው) ነበር፡፡ ጢጣ የወታደር ካምፕ ውስጥ የሚኖር፡፡ አሁን የወሎ ቴሪሼሪ ኬር ሆስፒታል የሚሠራበት፡፡ ይህ ሰው የምሥራቅ አማራ (ከአፋር ክልል የተወሰኑ ዞኖችን ጨምሮ) የብሔራዊ ደኅንነት ተጠሪም ኃላፊም ነበር፡፡ አብረውት የሚሠሩ በመከላከያ ሥር የነበሩ የደኅንነት ሠራተኞችም ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ አይስምሙም ነበር አሉ፡፡
ይህ ኮሌኔል ውስኪ ከመጠጣት እና ካራምቡላ ከመጫወት ባለፈ ዋና ተልእኮው የሚመስለው ለዘመናት አብሮ፣ ተዋዶ፣ ተፋቅሮ የኖረውን የደሴን ሙስሊምና ክርስቲያን ማጣላት ነበር፡፡ የብዙ ሙስሊም ዑለማዎችን ቤት፣ ሱቅ፣ ይገኙበታል የተባለን አድራሻ እያንኳኳ ብዙ ነገር ለመሸረብ ሞክሯል፡፡ እንደው አብሮ አደግ፣ ጎረቤት ክርስቲያን ወንድምና እህት ጋር ለማጋጨት ብዙ ጣረ፡፡ በዚህ በኩል ምንም ጠብ ሳይልለት ቀረ፡፡ አልተሳካለትም እንጂ!
የዞኑን እና አንዳንድ የከተማውን አመራሮችን ስም በመጥቀስ ለብዙዎች መጥፎ መጥፎ ዜና ነዛ፡፡ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ፡፡ በወቅቱ የክልሉ የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደግሞ አቶ ከበደ ጫኔ ነበሩ፡፡ ሁኔታውን ያውቁ ነበር አሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የጢጣው ኮሌኔል ባሰበውና ባቀደው ልክ ባይሆንም የተወሰነ ግጭት ተፈጠረ፡፡
ኮሌኔሉ ከዚያ አካባቢ ተነስቶ ወደ አፋር ከተዛወረ (?) በኋላ ሼህ ኑሩ ከሸዋበር መስጊድ ሲመለሱ ተገደሉ፡፡ የግዲውን ዘጋቢ ፊልም አሁን የተዘጋው ኢኤንኤን (ENN) ቴሌቪዥን ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረው ሰው ደሴ መጥቶ አዘጋጀ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተላለፈ፡፡
አሳዛኙ ነገር የጢጣው ኮሌኔል በየቤታቸው ሌት ከቀን ሲመላልስባቸው የነበሩት ሙስሊም ወንድሞቻችን ኋላ ላይ እንዲሁ በሐሰት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ኮሌኔሉ ምን ምን እንዳደረገ፣ ምን እያወራ ማን እንዲታሠር እንዳደረገ አይታወቅም፡፡ አንዳንዱ ሴረኛ የሚደግፍ መስሎም ለወንጀል ክስ የሚሆን ድርጊት ያቀነባብር ይሆናል፡፡ በአገራችን ምን ያልተሠራ መንግሥታዊ ድራማ አለ?
በዚያን ወቅት ደሴ ከተማ የነበሩ አንዳንድ የጸጥታና የፖሊስ አመራር አሁንም እዚያው አሉ፡፡ በወቅቱ እንደዚያ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የማን አባት ገደል ገባ ከማለት ያለፈ በጎ ተግባር የሌላቸው፡፡ ምናልባትም አብረው አቀናባሪ ባይሆኑ ነው?
ደሴን አሁን ላይ ለዚያውም ተመልሶ ሸዋበር መስጊድ አካባቢ ችግር ለመፍጠር ከጀርባ ሆኖ የሚያሽከርከር ሊኖር እንደሚችል ለመገመት የሚያስችሉ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡ የሆነው ሆኖ እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
የደሴ ሙስሊም ኅብረተሰብም ሆነ ክርሰቲያኑም በመረባረብ እንዲህ ዓይነት ነውጥ ዘሪዎችን ለፍትሕ ለማቅረብ ይረባረብ! የጢጣው ኮሌኔል አሁን በዚያ አካባቢ የለም፡፡ አዲስ አበባ ካራምቡላ ሲጫወት ይውላል አሉ፡፡ ከሌላ የጢጣው ኮሌኔል ዓይነት ሰዎች እራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ምክር ሁሉ ለበጎ ላይሆን ይችላል፡፡
(ኮሌኔሉን ደሴ በነበርኩበት ጊዜ በመልክ አውቀዋለሁ፡፡ ከላይ የጻፍኩት መረጃ ያደረሰኝ ግን በወቅቱ ጧት ማታ ሰይጣናዊ ምክር ለመስጠት ከመረጣቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ያኔም የኮሌኔሉን ምክር አልተቀበለውም ነበር፡፡)
(በውብሸት ሙላት)