ሕዝቤን ላናግር!

(በታምራት ነገራ) ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በሴሜን አሜሪካ የኢትዮጲያኖች የስፖርት ፌደሪሽን በሚያዘጋጀው በዓል ላይ በመገኘትና በጁላይ 6 አርብ በኢትዮጲያ ቀን ላይ ንግግር ለማድረግ ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩ በቅድሚያ በፌዴሬሽኑ ያልታሰበበት በመሆኑ የጠ/ሚ አብይ አህመድን ጥያቄ ለመወያየት የፌዴሬሽኑ ቦርድ በነገው እለት በአስቸኳይ ተሰብስቦ ድምጽ ይሰጥበታል፡፡ ይህን የጠ/ሚ አብይ አህመድን በኢስፋና ጥያቄ የሰሙ የዳያስፖራ አክቲቪስቶች ቦርዱ የጠ/ሚ አብይ አህመድን ግብዣ ውድቅ እንዲያደርገው የቦርዱ አባላትን ስልክ በመበተን የቦርዱ አባላት ላይ ጫና እንዲደረግ ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፌ ኢስፋና ለምን የጠ/ሚ አብይ አህመድን ጥያቄ መቀበል እንዳለበት ያሉኝን ምክንያቶች እና እይታዎች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ይህ ለኢስፋና ትልቅ ድል ነው

ኢስፋና ኢትዮጵያውያን በዳያስፖራ ካፈሯቸው ተቋማት ውስጥ ግንባር ቀደም እና ምናልባትም እጅግ ጠንካራው ነው ማለት ይቻለል፡፡ ለረጀም ጊዜ ያለማቋረጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የመገናኛ ፤የመቀራረቢያ፤ ሞቷል ተብሎ የነበረ የአገር ልጅ ተገናኝቶ የሚላቀስበት፤ የልጅነት ፍቅር እነደገና የሚታደስበት እጅግ ኢትዮጵያዊ መድረክ ነው፡፡ ይህ መድረክ ለረጅም አመታት እራሱን ከፖለቲካው ገለል አድርጎ በመኖሩም ምክንያት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመወደዱ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡

ይህም ሆኖ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በዚህ የአገር ልጆች የአንድነት መገለጫ መድረክ ላይ በነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሳ ኢስፋናን ለማፍረስ ትልቅ እቅድ አውጥተው ነበር፡፡ እቅዱንም በሼክ አላሙዲን የፋይናስ ተደርጎለት ዘመቻው ተጧጧፈ፡፡ ሆኖም የህዝብን ልብ ብር አይለውጠውም ሆነ እና በአንድ ከተማ ውስጥ የኢስፋና ዝግጅት ስቴዲየም ሞልቶ መቆሚያ ቦታ ሲታጣ መለስ ዜናዊ እና ሼክ አላሙዲን የደገሱበት እስቴዲየም አንድ ሰው እንኳን ዝር ሳይልበት መቅረቱን ምስክር ሆነናል፡፡

ኢስፋና ሊያፈርሰው ከነበረው መንግስት እና ድርጅት ውስጥ በቃ በእናንተ መድረክ ተገኝቼ ልናገር የሚል መሪ ማግኘቱ ኢስፋና በግልጽ ማሻነፉን ያስመሰክራል፡፡ ኢስፋናም ከመንግስት/ ከገዢው ፓርቲ ገለልተኛ የሆነ ብቻ ሳይሆን ተናንቆም ያሸነፈ መድረክ መሆኑን የሚያስመሰክር የድል አጋጣሚ ነው፡፡ ስለዚህ ኢስፋና የጠ/ሚ አቢይ አህመድን በእናንተ መድረክ ተገኝቼ ልናገር ጥያቄ ባይቀበል ያሸነፈውን ድል እንደመጣል ይሆንበታል እላለሁ፡፡

የኢስፋና ግብ ይሄን አይነት መድረክ መፍጠር ነው

በመንግስት እና ሕዝብ መካከል በተፈጠረ እጅግ አላስፈለጊ መቃቃር እና መራራቅ ሆኖ ነው እንጂ የአገራችው መሪ በዝግጅታቸው ላይ እነዲገኝላቸው ጥያቄ ማቅረብ የነበረባቸው የፕሮግራሙ አዘጋጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሰት ከፈጠረው ቁርሾ አንፃር ኢስፋና ግብዣ ሊያቀርብ አይችልም ነበር፡፡ ጠ/ሚ አብይም ይሕን ተገንዝበው በትህትና በመድረካችሁ ልገኝ ማለታቸው የተፈጠረውን የቁርሾ፤ቂም ጥላቻ እና መናናቅ ድባብ በእጅጉ ይሽራል፡፡

በአመለካከት ፤በፖለቲካ ፤የተለያዩ የአገር ልጆች እንደገና እንዲተያዩ እንዲወያዩ አዲስ እድል ከፍታል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢስፋና እስከአሁን ሲያደርገው ከነበረው ስራ ጋር የሚሄድ ፤የሚስማማ ፤የሚደጋገፍ እርምጃ ነው፡፡ ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ሕዝቤን ላናግር ከሕዝቤ ጋር ልነጋገር ፍቀዱልኝ ሲሉ ኢስፋና ካለው ኢትዮጵያውያንን የማቀራረብ ግብ አንጻር ጉዳዩን አፋጥኖ ለጠ/ሚ አብይ ጥያቄ በመልካም ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ዝግጅት ላይ የክብር እንግዳ ሆኖ ቀድሞ የተጋበዘው ጀግናው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ እና ጠ/ሚ አብይ አህምድ በአንድ መድረክ ላይ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረው እነሱም ቁጭ ብለው የተለያየ ሀሳብ ይዘው ስለአገራቸው እንዲያወሩ እንዲነጋገሩ ከማስቻል የበለጠ ኢትዮጵያውያን እንዲቀራረቡ የማስቻል ድል አለን? የኢስፋና ግብስ የህ አይነት ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆን አይደለምን?

ይሄ ለኢስፋና ትልቅ ክብር ነው

በአንድ ዝግጅት ላይ የሀገር መሪ ሲገኝ ከሀገር መሪው ጋር አብሮ የሚንቀሰቀሰው የሚዲያ ፤የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ፤ የፕሮቶኮል ኃይል እና ግርማ አብሮ ይመጣል፡፡ እስከአሁን ኢስፋና ዝግጅቶቹን በሚያዘጋጅባቸው ከተማዎች ሁሉ የከተሞቹ ከንቲባዎች፤ የግዛቶቹ ሴናተሮች እና ገቨርነሮች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳሽነት እና ተደናቂነት ተደማጭነት አግኝቷል፡፡
ኢስፋና የጠ/ሚ አቢይ አህመድን ጥያቄ በመልካም ቢያስተናግድ ግን ከዚህ በፊትም አይቶትም ሰምቶትም የማያውቀውን እና ለረጅም ተከታታይ አመታት የሚከተለውን የሚያተርፍበትንም ፖለቲካዊ ማሕበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሞገስ በአሜሪካውያን እና በአሜሪካዊ ተቋማት ፊት ያገኛል፡፡ ሁል ጊዜም እንደተለመደው መንግስታቸው ያሳደዳቸው፤ ከመንግስታቸው የተጣሉ ከሚል አሰልቺ ተረክ አዙሪት አውጥቶ እነዚህ እኮ በመንግስተቻው እውቅና የተሰጣቸው መንግስታቸው ያከበራቸው ናቸው መባል በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ይሄ የተረክ ለውጥ እና አብሮት የሚመጣው የኢኮኖሚ ለውጥም ለኢስፋና ብቻ ሳይሆን ለመላው ዳያስፖራ የመዳረስ አቅምም አለው፡፡

ታሪካዊ አጋጣሚ አያምልጠን

የቀድሞው ነገስታቶቻችን ተወደዱም ተጠሉም ገበሬው የተናገረውን አዝማሪው የዘፈነውን፤ ወታደራቸው ተናገረውን፤ ጭሰኛቸው ያንሾካሸከውን፤ ካሕናቶቻቸው የተቀኙትን የሚያደምጡ ከእነሱም ጋር የሚከራከሩ የራሳቸው ከሕዝባቸው ጋር የመነጋገሪያ መድረክ ዘይቤ የነበራቸው ጠቢቦች ነበሩ፡፡ ከአብዮት በኋላ ያየናቸው የሀገራችን መሪዎች ግን ሕዝበ ሊያገኛቸው፤ ሊያናግራቸው ቢፈልግ እንኳን ከሕዝብ የሚሸሹ ፤እነሱ እራሳቸው መቶ በመቶ በተቆጣጠሩት መድረክ ካልሆነ በነፃ መድረክ ላይ ቀርቶ ተራ የእድር መድረክ የሚሸሹ ድንቡር መሪዎች ናቸው፡፡

ጠ/ሚ አብይ አህምድ ሌላው ሁሉ ቢቀር ይህን የአብዮት አመጣሽ ባሕል ሰብረው በእናንተ መድረክ ልገኝ የማለታቸው ብቻውን ምን ያህል የለውጥ ታሪካዊ አጋጣሚ እጃችን ላይ እንዳለን ያስመሰክራል፡፡ ይህ ሕዝብ እና መንግስት ስደተኛ እና በባለ አገር መካከል የማቀራረብ የታሪክ አጋጣሚ ፈጸሞ ላይመለስ ይችላል፡፡ ይሄ ልዩ ድልድይ መገንባት ታሪካዊ አጋጣሚ እውን እንዲሂሆን ግን ጠ/ሚ አብይ ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ኢስፋና የጠ/ሚ አብይ አሕመድን ጥያቄ በበጎ በመመለስ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ አሻራውን ያስፍር፡፡

በጠ/ሚ አብይም ሆነ ገዢው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች በዝግጅቱ ወቅት ስርአት ባለው መልኩ ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙበት የሚያንጸባርቁበት ስፍራ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ለተወሰኑ አክቲቪስቶች ዘመቻ ፤ዛቻ እና ጫጫታ ሲባል ብቻ ከሀገራችን መሪ ጋር በክብር የመነጋገር አጋጣሚ ማጣት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም ኢስፋናንም የሚመጥን እርምጃ አይደለም፡፡

አዎ እኔን ጨምሮ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ከመንግስታችንም ሆነ ከገዢው ፓርቲ ጋር ብዙ ብዙ አጀንዳዎች አሉን፡፡ ሁልም አጀንዳዎች መልሱ ግን ዘመቻ አላናግርም አንነጋገርም የሚል ጫጫታ አይደለም፡፡ ለመጮህም ስፍራ እና ጊዜ አለው ለመነጋገር አና ለመደማመጥም ስፍራ እና ጊዜ አለው፡፡ የዳያስፐራ ማሕበረሰብ ከዚህ በኋላ ከመንግሰት እና ገዢው ፓርቲ ጋር ላለው በርካታ ውይይት፤ ክርክር እና ድርድር ይህ እነደውም በጎ ታሪካዊ አጋጣሚሚም ነው፡፡ ኢስፋናንም ወደ ታላቅ ማሕበራዊ መድረክ ከፍ የሚያደርገው አጋጣሚ ነው እላለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!