በወልቂጤ ከተማ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ

በደቡብ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤ ከተማ ለወራት ላጋጠመ የውሃ ችግር ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የሰዎች ሕይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ ያጋጠመው የውሃ ችግር ለረጅም ጊዜም በመቆየቱ ነዋሪዎች ብሶታቸውን ለማሰማት ዛሬ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ከተማዋ የውሃ ልማት አስተዳደር ቢሮ ባቀኑበትም ወቅት ነው የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ እርምጃ የወሰዱት።

በዚህም እስከ ሦስት የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸው፣ ሌሎች አምስት ወጣቶችም ጉዳት ደርሶባቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ‘ውሃ ይሰጠን’ በሚል በወልቂጤ ከተማ የውሃ ልማት አስተዳደር ቢሮ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን እያሰሙ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና በሰልፉ ላይ የነበሩ ነዋሪ ገልጸዋል።

ሰልፉ ሰላማዊ እንደነበር የጠቀሱት ግለሰቧ መሃል ላይ ባላወቁት ምክንያት “በፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ተከፈተብን” ብለዋል።

“ተኩሱ ለምን እንደተጀመረ ይሄ ነው ማለት አልችልም” በርካቶች ለተባባሰው የውሃ ችግር እልባት ይሰጠን በሚል ባዶ ጀሪካን ብቻ ይዘው በሰላም እየጠየቁ ነበር ብለዋል።

ተኩሱ ሲጀመር ነዋሪው ቢሸሽም የተጎዱ እና የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ነዋሪዋ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።