በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቁር በመልበሳቸው ምክንያት አገልግሎት ተነፈጉ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ከተጀመረው የነነዌ ጾም ጋር ምዕመናን ጥቁር በመልበስ ምህላ እንዲያደርጉ ባዘዘችው መሠረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ሰዎች ይህንን እየፈጸሙ ነው።

ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የታወጀው ከሁለት ሳምንት በፊት ከቤተክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት ውጪ ነው በተባለ ሁኔታ ሦስት ጳጳሳት 26 ኢጲስ ቆጶሳትን መሾማቸውን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶችን መሠረት በማድረግ ነው።

ነገር ግን ይህንን የሲኖዶሱን ትዕዛዝ ተግባራዊ ያደረጉ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ወከባ እና እንግልት እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች መታሰር እንዳጋጠመ የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ሠራተኞቻቸው ጥቁር ልብስ እንዳይልብሱ በቃል እና በጽሁፍ እያስታወቁ መሆናቸውን እንዲሁም ጥቁር የለበሱ ተገልጋዮችን አናስተናግድም ያሉም እንዳሉ ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።