መወጣጫውን የሚማግድ ማምለጫ በር የለውም!

(እ.ብ.ይ.) ወዳጄ ሆይ…. አባቶቻችን፡- ‹‹ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ›› የሚሉት አባባል ትልቅ ትርጉም ያለው አባባል ነው፡፡ በራሳችን ላይ ባለማወቅ አጥር የምናበጅ ብዙዎች ነን፡፡ የልባችንን አጥሩን አጥብበን ጠብበን እንቀራለን፤ የሃሳባችንን ቅጥሩን አሳንሠን አንሠን እንቀራለን፣ አስተሳሰባችንን አሳጥረን አመለካከታችን አጥሮ ይቀራል፡፡ አሻግረን አለማየታችን ገደሉን እንዳንሻገር፣ ውጣውረዱን እንዳናልፍ ያደርገናል፡፡ ሹፌር አርቆ ማየት ስራው ነው፡፡ ምክንያቱም ከርቀት የሚመጡ ሌሎች መኪኖችን፣ እንስሳቶችን፣ ሠዎችን ዓይቶ የማዳን ውሳኔ ከወዲሁ ያደርጋልና፡፡ የሠው ልጅም የሕይወት መኪናውን የሚያሽከረክር የራሱ ሹፌር ነው፡፡ በሹፍርናው የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ለሕይወቱ መድህኖች ናቸው፡፡ የደቂቃ ውሳኔ የሕይወት ገንዘብ ሊያስከፍለው ይችላልና፡፡ ህይወትህን በጥንቃቄ አሽከርክር!

እራሱን በራሱ ባለማወቅ የሚያጠምድ አርበኛ በዚህ ዘመን በዝቷል፡፡ አይጥ ሠው ባጠመደበት ወጥመድ እንጂ በራሱ ወጥመድ አይደለም ተይዞ ጉድ የሚሆነው፡፡ ብዙዎቻችን ግን ወጥመዳችን አስተሳሰባችን ነው፡፡ የእግር ብረት ሠንሠለት በሕይወታችን የምናስገባው በራሳችን አመለካከትና በጊዜያዊ ምቾት ቀመር ነው፡፡ ጠላት ከሚያጠምደን ይልቅ ራሳችንን የምናጠምደው እንበዛለን፡፡ በራሱ ላይ ክብሪት የሚጭር ምን ዓይነት ሠው ነው??

ለጊዜያዊ ምቾት ብለህ ቋሚውን ህይወትህን አታበላሽ፡፡ ሕይወት ብዙ እድሎችና መልካም አጋጣሚዎች ያሏት ብትሆንም ለጊዚያዊ የስሜት እርካታና እና ለደቂቃ ምቾት ብለህ የሕይወት መንገድህን አትዝጋ፡፡ በስሜት የምታደርጋቸው ነገሮች ውስጣዊ ሕሊናህን የሚያረካ ካልሆነ ጠንቀቅ ማለት ይበጅሃል፡፡ ልብህን ለሚሞላ ዛሬንና ነገን ለሚያስደስትህ ነገር ራስህን ወጥር፡፡ ለደቂቃ ብለህ የዓመታት ህይወትህን አታባክነው፡፡

ጊዜና ወንዝ አንድ ነው፡፡ አሁን የሚጎርፈው የወንዝ ውሃ ትናንት የጎረፈው ዓይነት አይደለም፡፡ ጊዜም እንደዛው ነው፡፡ በሃያ ዓመትህ የነበረው ጊዜ በሠላሳ ዓመትህ ከሚኖረው ጋር አልተገናኝቶም ነው፡፡ በሃያ ዓመት መስራት የሚገባህን ሳትሠራ በሠላሳ ዓመትህ ልስራው ብትል አንድም ይከብድሃል፤ አንድም የሠላሳው ዓመት ስራህን ይሻማብሃል፡፡ በጊዜው ያላቁላላኸው ሽንኩርት ለመብል የጣፈጠ እንደማይሆነው ሁሉ በሕይወት ጊዜህም የተሠጠህን ነገር በጊዜው ካልከወንከው ወይ አይበስልም አልያም ያራል፡፡ በጊዜው ያልተማሠለ ሃሳብ አይበስልም!

የሚገርመው በሕይወታችን ጉዳይ ሳይኖረን የምንቸኩልበት ነገር ብዙ ነው፡፡ ለውጥ ለማናመጣበትና ለማይጠቅመን አርቲቡርቲ ውዱን የሕይወት ጊዜአችንን እናባክናለን፡፡ በቸልተኝነት ጣጣ በኋላ የምንከፍለው ሂሳብ የማንችለውን ይሆናል፡፡ በቸልታ ዛሬ ላይ የምናደርጋት ስህተት ወይም ጥፋት ነገ ዋጋዋ ውድ ነው፡፡ ጊዜ በራሱ የሚመለስ ባለመሆኑ በጊዜ ውስጥ ልናገኛቸው የሚገቡ እድሎችን በቸልታ ከእጃችን ያመልጣሉ፡፡ ጊዜንና ዕድልን ወደኋላ ማጠንጠን ባለመቻሉ ያመለጠን እንዳመለጠን ይኖራል፡፡

ወዳጄ ሆይ….. ለጊዜያዊ ምቾት ብለህ የእድል መሰላልህን አትማግድ! መወጣጫውን የሚማግድ ማምለጫ በር የለውም!

ቸር ጊዜ!
______________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.