“የአንድነት ኃይሉ” ዕጣ!

(ጌታቸው ሽፈራው) አንድ እውቅ ፖለቲከኛ ወደ አማራ ክልል አቅንቶ ነበር። ብዙ ዋጋ ከፍሏል። “እስኪ አማራ ያድንህ” ተብሏል። በእስር ቤቶች የሚፈፀሙትን የዘር ጥቃቶች አይቷል። ይህ ፖለቲከኛ ዋጋ መክፈሉ ብቻ ሳይሆን ቅንም ነው። በሕዝብ ላይ ክፉ ባያስብም “አማራው የሚጎዳው በኢትዮጵያዊነቱ ነው” እያለ ስሙ እየተጠራ የሚገረፈው፣ የሚዘረፈው፣ የሚገደለውን ሕዝብ ቁስል መናገር የማይደፍረው የአንድነት ሀይሉ አባዜ አለበት።ይህ ቅን፣ ግን ስሙ እየተጠራ በዓለም አለ የተባለው ጭካኔ ሁሉ የተፈፀመበትን የአማራ ሕዝብ መደራጀት የለበትም “አማራ አማራ” መባል የለበትም የሚል ሰው እንደተፈታ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር አግኝተን አውርተነው ነበር። እዚሁ ብዙ የተሰቃዩ እያሉ ይህ ቅን ሰው የሚያወራን ስለ ጋንዲና ማንዴላ ነው። ያም ሆኖ “አማራ አማራ መባል የለበትም” በሚል አቋሙ ፀንቷል። የሕዝብን ቁስል በቀጥታ አለመናገር ዋጋውን ግን አይቶታል።

ወደ አማራ ክልል ይሄዳል። ንግግር ያደርጋል። ሕዝብ ይህ የሚያከብረው ሰው የሚለውን ሰምቶ ፀጥ ይላል። ፖለቲከኛው ግራ ይገባዋል። ያ የሚያውቀው ሕዝብ አልሆንለት ይላል። የቆሰለ፣ ቁስሉ የበዛበት፣ ስሙ እየተጠራ መዘረፉ፣ መገረፉ፣ መገደሉን ሲያውቅ ተበድያለሁ ብሎ በግልፅ የሚናገር ሕዝብ ሆኗል። ያ ቅን ፖለቲከኛ ከኢትዮጵያ አንድነት ውጭ ሌላ መንገድ የለም ይል የነበረው አብዛኛው ሕዝብ ስለ አንድነት መጨነቁ “ነፍጠኛ፣ ገዥ፣ ትምክተኛ……” የሚል ፍረጃ፣ ፍርድም ያረፈበት ሕዝብ በመከራው ብዛት ብሔርተኛ ሆኗል። እናም ያ ፖለቲከኛ ህዝብ የተወገዘበትን አንድነት ጉዳይ ሲያወራ ሰሚ አላገኘም። ቅንነቱ በክፋት የታሰበበት ሕዝብ፣ ስለ ሀገር አንድነት የተወገረ ሕዝብ አሁን ሲወገር የሚጠራበትን ስም ይዟል። “አማራ ስለሆንኩ ነው የተበደልኩት” ብሏል። እና ያን ፖለቲከኛ መስማት አልፈለገም።

በክብር እንግድነት ከተጠሩት መካከል ቀዳሚ የሆነው ያ እውቅ ፖለቲከኛ ነው። ከእሱ ቀጥሎ በእስር ቤት ስማቸው እየተጠራ የተገረፉት ወጣቶች ንግግር አደረጉ። ሳያድበሰብሱ የሕዝብን ቁስል ተናገሩ። ሕዝብ የሚሰማውን ተናገሩለትና ለእውቁ ፖለቲከኛ ያልሰጠውን ድጋፍ በጭብጨባ ገለፀላቸው። ያ እውቀ ፖለቲከኛ ይበልጡን አዘነ። የሚናገሩት ወጣቶችን መውቀስ ጀመረ። “እንዴት እንዲህ ይላሉ!” አለ። እንዲያውም መድረኩን ጥየ እሄዳለሁ አለ። አረጋጉት።

ከፕሮግራሙ በኋላ የአደራሽ ውይይት ተደረገ። ፖለቲከኛውም ሕዝቡን “አፍሬባችኋለሁ፣ እንዴት እንዲህ ብሄርተኛ ትሆናለህ” አላቸው። በአዳራሹ የተገኙ ወጣቶችም “እናከብርሃለን፣ መንገዳችን ግን ተለያይቷል” ይሉታል። ስብሰባውን አቋርጦ ይሄዳል። እንዲያውም እሱ በክብር እንግድነት ጠርተው መጠቀሚያ እንዳደረጉት፣ ክርክራቸውንም እንደ ስድብ ነው የቆጠረው።

ይህ ቅን ሰው ሆን ብሎ የአማራ ሕዝብን ቁስል ለመደበቅ ፈልጎ አይመስለኝም። ሰውየው ቅንነት አለበት። ምን አልባት ፖለቲካውን አልተረዳው ይሆናል። በአንፃሩ ሆን ብለው የአማራውን ቁስል የሚደብቁ፣ በደሉ ቢሰማ ኢትዮጵያ የምትበተን የሚመስላቸው፣ ከዛ ሲያልፍ ደግሞ የአማራውን ሕዝብ ከመጠቀሚያነት ውጭ ሉአላዊ ድንበሩን ሲያስከብር ሲሰዋ እንኳ እውቅና መስጠት የማይፈልግ፣ ቁስሉን መናገር፣ ስሙን መጥራት የማይፈልገው፣ በሂደት ጥላቻ ያዳበረ፣ ሕዝብን የፈረጀ የአንድነት ኃይልም አለ።

ሕዝብ ያን ቅን ፖለቲካ የሸኘበት መንገድ ለሌላውም መልዕክት ነው። ይህን የሚያከብረውን፣ መጠቀሚያ ያላደረገውን ሰው እንዲህ ሲሸኝ መጠቀሚያ ያደረገውን፣ አድበስባሹን፣ የሕዝብን ስም መጥራት የማይፈልገውን የአንድነት ሀይል ደሴ፣ ደብረብርሃን፣ ጎንደር፣ ባህርዳር ላይ ምን እንደሚገጥመው ግልፅ ነው። ያ ቅን ፖለቲከኛ “አማራ አማራ አትበሉ” እያለ የተበሳጨበት ወጣት በአማራ ሕዝብ ላይ መግለጫ ያወጣውን፣ በደሉን ለመናገር አፉን የሚይዘውን የአንድነት ሀይል ጋር ሲገናኝ ማየት ነው።

የአንድነት ኃይሉ ዋና መንቀሳቀሻው አማራው ነው። የዚህም ሕዝብ በደል ግን ማናገር አፉን ይይዘዋል። በዚህ መንገድ የት እንደሚደርስ ማየት ነው። በእርግጠኝነት ከዛ ቅን ፖለቲከኛ የከፋ ነገር እንደሚያጋጥመው ግልፅ ነው። የአንድነት ኃይሉ የአማራውን ቁስል መናገር እንደ ነውር እየቆጠረ፣ በዚህ ሕዝብ መሃል እንቀሳቀሳለሁ ሲል የሚያጋጥመው ከቅኑ ፖለቲከኛ የባሰ እንደሚሆን ግልፅ ነው።

ያን ቅን ፖለቲከኛ የገጠመው ፈተና የአንድነት ሀይሉ ያበላሸው ነው። የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የፖለቲካ መስመሩ መጥፎ ሆኖም አይደለም። የአማራ ሕዝብ ስለ አንድነት ባደረገው አስተዋፅኦ የገዥዎቹ አፀፋ ቅጣት ሆነ። ነገር ግን የአማራውን ሕዝብ አሁን የያዘውን አቋም ከገዥዎቹ ቅጣት ብቻ የመጣ አይደለም። የአንድነት ሀይል ነኝ የሚለው ተቃውሞ ሀይል የፈፀመበት ክሕደት ጭምር አሁን ያለውን የፖለቲካ አቋም ላይ አድርሶታል። የቆሰለን ሕዝብ በደል የመደበቅ ያህል በደል፣ ክህደትም የለም! ይህን የአንድነት ኃይል ዕጣ የምናየው ይሆናል!