የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ኦዴፓ በፌደራል ስርዓቱ ላይ ዘመቻ ተከፍቷል አለ።

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ኦዴፓ ለፌደራል ስርዓቱና ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር እየሠራ ቢሆንም በተቃራኒዉ «አሁን ያለዉ መንግሥት የፌደራል ስርዓቱን ሊያፈርስ ነዉ»፣ «ሕገመንግሥቱ እየተናደ ነዉ» በሚል የተሳሳተ ዘመቻ መከፈቱን አመለከተ። ፓርቲው ትናንት ባወጣው መግለጫ ኦዴፓ በፌደራል ስርዓቱ እንደማይደራደርና ወደፊትም የኦሮሞ ህዝብን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠራ ገልጿል። የአዲስ አበባና የአፋን ኦሮሞ ጉዳይም የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች በመሆናቸዉ ለመመለስ እንደሚሠራ የፓርቲዉ ማዕከላዊ ኮሚቴ የህዝብ አስተያየትና ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለDW ገልፀዋል። ኦዴፓ «ዘመቻ ከፈቱ »ያላቸዉን ወገኖች ማንነት ግን በውል አልገለፀም።