እውነትን የማያጎብጥ ዘለፋ 

(በሳምሶን ሚኪያሎቪች)

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ከስር የተመለከተውን ጽሁፍ ማስረጃ አድርገው አዲሱ ብሄረተኝነት ወዴት እየሄደ ነው የሚል ጥያቆ አነሱ። መለስ ጨናዊ እወክለዋለሁ ያለውን ህዝብ ‘ወርቂ ህዝቢ’ ፣ ጃዋር መሀመድ ‘ኦሮሞ ይቅደም~Oromo First ‘ ሲል የጮሁ ” ይሰቀል” ያሉ ወገኖች ዛሬ አንዱ ተነስቶ የገዛ ብሄሩን ‘የእግዜያብሄር የበኩር ልጅ’ ብሎ ሲያሞካሽ እርሱን ትተው ፕሮፌሰሩን መወረፍ ያዙ።

የግለሰቡን ጽሁፍ ‘አማራ’ የሚለውን በሌላ ብሄር ተክቼዋለሁ። ሚዛናችንን ምናልባት ልክ ያደርገው ከሆነ። ጎሰኝነት የሰውን ስህተት የሚያሳይ ራስን ‘የእግዜር የበኩር ልጅ’ እያሰኘ የሚያንቆለጳጵስ ክፉ ደዌ ስለሆነ ነው ምክንያቴ ።

«ትግራዋይ ብሄርተኝነት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ስጋት የማይሆንበት ተጨማሪ ምክንያት የብሄረሰቡ ትክለ ስብዕና ነው፡፡ ተጋሩ የጥበብ መሃንዲስ ነው፣ ታሪክ ሰሪ፣ ድንበር አስከባሪ፣አሰተዋይ መሪ ነው፡፡ ለአከርካሪው ሲቃጡት አናት የሚያፈርስ የጀግኖች አውራ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጰያ ትግራዋይ የአግዜር የበኩር ልጅ ነው፡፡ በሃይማኖቱ፣ በቁርጠኛነቱ በደግነቱና በትዕግስቱ ያሰበበት ደራሽ ነው፡፡…..»

ደግሞ ግዮኒዝም ምናምን የሚል ቅብዥር ዶሴ የጻፈው ምስጋናው የሚባል ብሄረተኛ የጻፈውን እናንብብ ፤

” አማራ የምርጥ ህዝብነት ወይም የአምላክ ህዝብነት ባህሪያትና ትውፊት ካላቸው ህዝቦች አንዱ መሆኑን ከአንቶኔኑ ትንተና እንረዳለን። …. እንዲያውም አፍሪካ ውስጥ የምርጥ ህዝብነት አስተሳሰብ እና ይሄም አስተሳሰብ በመላው አለም የሚታወቅለት ህዝብ አማራ ብቻ ነው። ” (really ?ከላይ የተገለጹት ጽሁፎች አንድ የትግራይ ፣ ኦሮሞ አልያም ሌላ ብሄር ሰው ቢጽፈው አቧራ አይጨስም ነበር ?

የብሄረተኞች እናታቸው አንድ ነች። የኦሮሞ ብሄረተኛ ውስጥ የምታገኙትን ባህሪ የአማራ ወይም የትግራዩ ፣ እልፍ ሲልም የእንግሊዝ ፣ አሜሪካ ቀኝ መንገደኛ ጋር ታገኙታላችሁ። ለብሄረተኞች እነርሱ ቅዱስ ሌላው እርኩስ ፣ እነርሱ የእግዜር በኩር ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ ፣ የእነርሱ ምድር ማርና ወተት የሚፈስባት የሌላው ምድረ በዳ ሆና ነው የምትታሰባቸው። ለዛሬ ሁሉም ጋር ስላሉት ባህሪያትና ሀሳብን የመድፈቂያ ስልቶች ላውሳ ፤

፩. ተከለሰውነት ማጉደፍ (character assassination) ። አንዳንዶቻችን አዲሶች ብሄረተኞች ብርሃኑ ነጋን በንዋይ ፍቅር ፣ ታማኝ በየነ በእምነት አጉዳይነት ፣ ፕ/ር መስፍን በአማራ ጠልነት ሲከሰሱ ‘ምን እየሆነ ነው?’ ጆሮአችን ነው ወይስ ቅዠት ይሆን ስንል ደጋገመን ጠይቀናል። ባለፉት ሁለት ሶስት አመታት ዘለፋና ስድብ ፓለቲካ የሆነበት ለሀገር ትልቅ ውለታ የዋሉ ‘አንተ ~አንቺ’ የተባሉበት የግሪምቢጥ ጊዜ ነበር።

ብሄረተኞች ስም ማብከትን ለምን ይወዱታል ለሚለው መልሱ ያለው የብሄረተኞች መልዕክተኛውን የመግደልና መንጋውን የመበተን ስልት ላይ ነው ያለው። የኢትዮጵያዊነትን ርዕዮት ለማጠልሸት የኦሮሞና ትግራይ ብሄርተኞች ምኒልክን የራሳቸውን ወገን ጎበና ዳጬና ጃጋማ ኬሎን ሳይቀር ያዋርዱ እንደነበረው ነው (ሹማምንቱ ፍጹም ናቸው እያልኩ አይደለም) ። ጎሰኞች የኢትዮጵያዊነት ርዕዮትን ለማጥፋት ጀግኖቻችንን ፣ የታሪክ ምልክቶችን ፣ ተቋማትን ባንዲራችንን ሳይቀር ሲያዋርዱ እናውቃለን ~መሰባሰቢያ ማንነቶቻችንን ማስጣል ወደ ብሄር ቆጠራ እንደሚወስደን ስለሚያውቁ ነው።

ከሶስት መቶ ምናምን ገጽ የብርሀኑ ነጋ መጽሀፍ ገጽ 72 ላይ ያለች ሀረግን ጠንቁሎ ሰውየው አማራን ይጠላል የሚልህ ጎሰኛ ሰባት ጸበል ብታጠምቀውም ሰውየውን አይፋታውም። ግተውታላ ~ ጎሰኝነቱን! ታማኝ በየነን በአማራ ጠልነት የሚከስ መደዴ የጎሰኝነት ዛሩ እስኪበርድ ቸል ትለዋለህ እንጂ የታማኝን የ27 ዓመታት ኢትዮጵያዊ ተጋድሎ አታወሳውም !!!

ኢትዮጵያዊ ብሄረተኞች ለአዲሶች የመለስ ዜናዊ ግርፎች የምንነግራቸው አብይ ነገር የተሰባሰብነው ንቅንቅ በማይል ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ መርሆ ላይ ስለሆነ ተክለሰውነት ገደላው አይንደንም ነው ። ኢትዮጵያዊነት ሲመቱት ይጠብቃል እንዲሉ !!!

፪. ሌላው የብሄረተኞች የጋራ ስልት መረጃ ማዛባት (misinformation) ነው። በ1980ዎቹ የትግራይና ኤርትራ ልሂቃን (የኦነግ ሰዎችን ጨምሮ) ኢትዮጵያ የአማራ ኤምፓየር ነች የሚል ነጭ ውሸት ይነዙ ነበር። የገበሬ ጦራቸው ‘የአማራን ገዢ’ መደብ የሚል የዕብለት ፕሮፓጋንዳ ጠዝጥዘውት የአማራ መንደሮች በወርቅ ያጌጡ እስኪመስለው አዕምሮውን ሸብበውት ነበር። በዚህ ግራ አጋቢ የሀሰት ዘመቻ ወቅት ከአንድ ወገን ከኦሮሞ ይወለዳሉ የሚባሉት ኮ/ል መንግስቱ ሳይቀር እረ እናንተ የምታስቡት አይነት በጎሳ የተደራጀ ‘አም ~ሐራ’ የሚባል ብሄር የለም ሲሉ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።

ኋላ መለስ ዜናዊ አራት ኪሎ ሲገባ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምም የትግራይ ብሄረተኞች እንደሚያስቡት ያለ በብሄር የተደራጀ ፣ በገዢ ብሄርነት የሚፈረጅ አማራ የሚባል ብሄር የለም ሲሉ ተከራክረዋል። አነብናቢዎች እንደሚነግሩን ይህ ማለት አማራ የሚባል ዘውግ የለም የሚል የቂል መከራከሪያ አይደለም ። ይልቅ የጎንደር አማራ ከጎጃሙ አልያም ከሸዋው አማራ ጋር በብሄር ርዕዮት ተሳስሮ የማለሊት ሰዎች እንዳደረጉት ሀገር ልግዛ አላለም ፣ የአማራ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የነበረው ተሳትፎ ዘውግ ዘለል ነው ነበር ያሉት ፕ/ር መስፍን።

የዛሬዎቹ የዘውግ ፓለቲካ ቀሻቢዎች (ethnic entrepreneurs) ይሄ አይጠፋቸውም ። ነገር ግን ሰው የሚያሰባስበው ‘የሉም ተባልን’ ስለሆነ ላለፉት 27 አመታት አማሮች ላይ ግፍ በተፈጸመ ቁጥር ሲጮሁ የነበሩት አዛውንት ውለታ በስድብና ዘለፋ እየተከፈለ ነው ። እነ በረከት ስምኦን በተከታታይ የሬዲዮና ጋዜጣ ስም ማጥፋቶች ያላሸነፏቸው ሰው ሙቅ እየቀቀለ በሚሳደብ ወፈ ሰማይ ይሸበሩ ይመስል?

እናጠቃለው። የኢትዮጵያን ፓለቲካ የምንከታተል ሰዎች ከሰሞኑ የአማራ ብሄረተኝነት በፊት በትግራይ ፣ ኦሮሞ ፣ ሲዳማ ወዘት ትዕይንት የዘውግ ፓለቲካን አይነተኛ ባህሪያት ተምረንበታል። ብሄረተኝነት በራሱ ክፉ ባይሆንም የክፉዎችና ዘረኞች መደበቂያ እንደሚሆን እናውቃለን።

ፕ/ር መስፍን እንዳሉት መስፈሪያ ሚዛናችንን የሰሞኑ አዋጭ የፓለቲካ ምንዛሬ (currency) የቱ ነው እያልን የምንቀይር አይደለንም። ስለሆነም መለስ ዜናዊ ‘ወርቂ ህዝቢ ‘ ሲል ፍልጥ ዘረኛ ያልነው ሰዎች ሌላው ተነስቶ የእኔ ብሄር ‘የእግዜር የበኩር ልጅ’ ነው ሲልም ያንኑ ብያኔ እንድንሰጥ ህሊናችን ያስገድደናል ፤ እውነትም በአጀብ ብዛት እንደማይመዘን ልናስታውስ እንወዳለን።

መልካም የስራ ሳምንት