በወንድወሰን ሽመልስ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ረፋዱን(ግንቦት 7) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለተሰበሰቡ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በስራዎቻቸውና አሰራር ዙሪያ ገለጻና ማሳሰቢያ ሰጡ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መድረክ ላይ የራሳቸውን ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ በዚሁ ጽሁፋቸውም የአመራር ጥበብን በተመለከተ ገለጻ አድረገዋል። የህዝበ አገልጋይ ምን አይነት ሰብዕና ሊላበስ እንደሚገባና ምነ አይነት አገልግሎት በምን አይነት ጊዜና ቦታ መስጠት እንዳለበትም በተለያዩ አብነቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለጻቸው ወቅት እንዳሉትም፤ ሳምንታዊው የካቢኔ ስብሰባ ከአርብ ወደ ቅዳሜ መለወጡንና ሚኒስትሮች አርብ በስብሰባ ስም ጊዜ ማባካን እንደሌለባቸውና መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ አሳስበዋል።
አገሪቷ እያደገች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አለብን ሲሉም አስታውቀዋል።
እያንዳንዱ የመንግስት አመራርም አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ እንደሚገባውም ዶክተር አብይ አሳስበዋል።
እያንዳንዱ ሚኒስትር ከዚህ በኋላ ለስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጭ አይደለም” ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት።
ከባለስልጣናት ጉዞ ጋር በተያያዘም ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም አገራት ትብብር እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ በኋላም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ከሚከታተሏቸው ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር የስራ ስምምነት መፈጸም እንደሚገባቸውና ስራቸውን በዚህ አግባብ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከስብሰባው በሁዋላ ባለስልጣናቱን ከአዳራሽ ይዘው በመውጣት በአጼ ሚኒሊክ፣ በአጼ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመን የተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው በቤተመንግስት የሚገኙና እስካሁን ድረስ ዝግ የነበሩ የተለያዩ ክፍሎችን አስከፍተው እንዲጎበኟቸው አድርገዋል።
በዚህም ባለስልጣናቱ የነገስታቱን የግብር ቤቶች፣ አጼ ሀይለስላሴ የተገደሉበትን፣ የደርግ ጄኔራሎች የተረሸኑባቸውን ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ጎብኝተዋል።
(ምንጭ ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)