ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ ታሪካዊ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ተናገሩ። የአሜሪካ – ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ረይነር እንዳሉት በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ወሳኝና ታሪካዊ ነው።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየወሰዷቸው ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች እንደሚያደንቁ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ለውጡ በኢትዮጵያዊያን መምጣቱ ጥሩ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሩ አሜሪካም ይህን ለውጥ ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካዔል በበኩላቸው በኢትዮጵያዊያንና በሰብአዊ መብት ተቋማት ይነሱ የነበሩ የሰብዓዊ መብት አያያዝና መሰል ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአንድ ቀን በሚቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ተቋማት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
(ምንጭ።- ኢዜአ)