የአንዳርጋቸው ቁጭትና “ምሁራዊ” ዕዳ

(መሐመድ አሊ መሐመድ)

“ነፃነትን የማያውቅ ‘ነፃ አውጭ'” በተሰኘው መጽሐፍ ሽፋን ላይ የምናየው ምስል ስጋው ያለቀና አጥንቱ የተፋቀ ህፃን በጣዕረ-ሞት ተይዞ ለለቅሶ የተከፈ አፉን ለመዝጋት እንኳን አቅም ሲያጣ ነው። ይህ ምስል ማንንና ምንን ነው የሚወክለው? አንዳርጋቸውስ ስለምንና ለማን መናገር ነው የፈለገው? ራሳችንን “በፖለቲከኛነት” የምንኮፍስ ሰዎችስ ህዝባችን ካለበት አስከፊ ሁኔታና ጎስቋላ/የኑሮ ገፅታ አንፃር ለትግሉ የሚመጥን ቁርጠኝነትና የሞራል ብቃት አለን ወይ?

ቁርጠኝነት ሲባል የወያኔን ሥርዓት መጋፈጥ ብቻ ሊመስለን ይችላል። አንዳርጋቸው ግን የችግሩን አድማስ የሚረዳው ከዚያም ባሻገር ነው። በመጽሐፉ ገፅ 4 “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ከወያኔ ጋር ብቻ የተሳሰረ ሳይሆን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቅ አጠቃላይ ችግሮች ጋር የተያያዘ ነው; የሚል ፅኑ እምነት አለኝ” ሲል ይሞግታል። ችግሩ “ከባህላችን; ከማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አደረጃጀታችን ጋር የተሳሰረ” መሆኑን በአፅንዖት ያመለክታል።

አንዳርጋቸው ለወያኔ የማይገባውን ቁመና የሚያጎናፅፈውን በሴራ ትንተና ላይ የተመሠረተ ቅኝት (orientation) የፖለቲካ “ነፈዝነት” ሲል ይደፍቀዋል። በአንዳርጋቸው እይታ; የሴራ ንድፈ-ሀሳብ (conspiracy theory) ለኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን የሚስማማ ሲሆን ውስብስብ ጉዳዮችን አቃልሎ ማቅረብና ወያኔን ያለ አቅሙ አገዝፎ ማየት ነው። (ገፅ 225) እንዳርጋቸው እንዳለውም በራሳችን ምናብ በፈጠርነው የወያኔ ጥላ ሥር በሴራ ትንተና ተጠምደን ከተራራ የገዘፉ አስፈሪ ችግሮች ከፊታችን ተገትረው ልናያቸው አልቻልንም።

አንዳርጋቸው ይህን ዝቅጠት ከደካማ “ምሁራዊ ባህል” ጋር ያይዘዋል። እንደእሱ ትንተና የሀገራችን ምሁራዊ ባህል “የማሰብን; የማሰላሰልን; የማጥናትንና የመመራመርን ልምዶች ከማዳበርና ከማስፋፋት ይልቅ; ሳይጠይቁ መቀበልን; መዋስን; መገልበጥንና መኮረጅን” የሚያበረታታ ነው። ይህ በባዶ የልታይ-ልታይ ባይነት አባዜ “የአስመሳይነትና የአጭበርባሪነት ባህል እንዲጠናከር አድርጓል።” ያስከተለው ቁሳዊና ሰብአዊ ኪሳራም በቀላሉ የሚሰላ እንዳልሆነ አንዳርጋቸው በትልቁ ያሰምርበታል። (ገፅ 43)

በዚህ ላይ “የሊበራል ዴሞክረሲ የፖለቲካ ባህሎች ባዕድ በሆኑባት; ግለሰቦችና ቡድኖች የመደራጀትና ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት አይተው በማያውቁባት ሃገር; የአመለካከት ልዩነቶች ከጉልተኛ ባህላችን ባመጣነው የግለሰብ ግትርነት; አልረታ ባይነት; ተጠራጣሪነት; ከማን አንሼ ባይነት; የሥነ-ልቦናዊ ግጋር ላይ እየተገነቡ; መቻቻልና መደማመጥ የሌለበት; መጥፋት ወይንም ማጥፋት ብቻ በምርጫነት የሚታዩበት” ሁኔታ መንገሱንና አጠቃላይ ውድመት ማስከተሉን አንዳርጋቸው በቁጭት ያትታል። (ገፅ 23)

በተለይ “ዘውገኛነት በመሠረተ-ባህሪው ለአድርባይና ከአውዳሚነት ጋር ቅርበት ላለው የሀገራችን ፖለቲካ በጣም የተመቸ ነው” ሲል ያስረግጣል – አንዳርጋቸው። “ዘውገኝነት” ይልሃል “ዝርዝር የፖለቲካ መሠረታውያን ላይ የተመሠረተ ጥናት አያስፈልገውም። ጥቃትና በደልን; መወለድና ዘርን አጣቅሶ የሚደረግ መሰባሰብ ስለሆነ በስሜታዊነት ነዳጅነት በቀላሉ ሊቀጣጠል ይችላል።” … “ዘውገኝነት የፈለገውን ቅብ ይቀባ; ዘረኝነትንና ጠባብነትን ከመሠረተ-ባህሪው ማጥፋት አይቻልም።” (ገፅ 228)

እናም ያስጠነቅቃል – አንዳርጋቸው። “ዛሬም ቢሆን ሥልጣን የመያዝ ዕድላቸውን አነስተኛነት አስልተው የፖለቲካ ትግላቸውን በአውዳሚነት ላይ የሚመሠርቱ ኃይሎች ከወያኔ ስህተቶች ብዙ መማር ይኖርባቸዋል” ሲልም ይመክራል። (ገፅ 309) መቼም ካለፉ ስህተቶቻችን እንዳንማር ካልተረገምን በስተቀር የወያኔን አውዳሚ አካሄድ ላለመድገም የአንዳርጋቸው ምክር ብቻ ከበቂ በላይ ነው።

አንዳርጋቸው የተጋፈጠው እውነት አድማሱ ሰፊ ነው። አንዳርጋቸው እየከፈለ ያለው የሌሎቻችንን “ምሁራዊ” ዕዳ ነው። እሱ አጉል “ልታይ ልታይ” የሚል አይደለም። እሱ ሁሌም በሥራው ላይ እንዳተኮረ ነው። እሱ የባከኑ ጊዜያትና ያመለጡ ዕድሎችን በቁጭት እያሰላሰለ በቀሪ ዕድሜው አንዳች ቁም ነገር ለመሥራት ደፋ ቀና የሚል “ብቸኛ” ባተሌ ነው።

አንዳርጋቸውን በ97 ምርጫ ወቅት በቅርብ አውቀዋለሁ። በተለይም ከምርጫው በኋላ በቅንጅት ላዕላይ ም/ቤት ስብሰባዎች ብዙ ተሟግተናል። ከአንዳርጋቸው ጋር በሀሳብ/በአቋም መለያየት ቢኖርም ሀሳቡን አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረትና ትጉህነቱን አለማድነቅ አይቻልም። አንዳርጋቸው ወደ ስብሰባ ሲገባ ከሌሎቻችን በተለዬ ሀሳቡን ሰንዶና ክርክሩን ደርዝ አስይዞ የመግባት ልምድ ነበረው።

አንዳርጋቸው በሰላማዊ መንገድ የመታገል አማራጮች በመጥበባቸው የትጥቅ ትግልን መምረጡ በሥራ ላይ ባለው ህግ “ወንጀል” ነው ቢባልም “የግንቦት 7 አባል” ተብለው የተከሰሱና የተፈረደባቸው በርካታ ሰዎች በይቅርታ/ምህረት ተፈትተዋል። ታዲያ ምነው የአንዳርጋቸው ጉዳይ እንዲህ ምጡ ጠና? አንዳርጋቸውን አስሮ በማቆየት ምን ማትረፍ ይቻላል?

የምታደርጉት ለማንም አይበጅምና አንዳርጋቸውን ፍቱ!!!