ፓለቲከኛ አብረሃ ደስታ ታሰሩ

ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣን አቶ አብርሐ ደስታ “ግጭት በመቀስቀስ” እና “ሕገ-ወጥ ሽጉጥ ይዞ በመገኘት” መጠርጠራቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ። አቶ አብርሐ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም እንደታሰሩ ሬውተርስ ዘግቧል።

ከመታሰራቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች ይደርሱባቸዋል ያሏቸውን ግፎች በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ዘርዝረው በመጻፍ ለዋና ከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አቤቱታ አቅርበው ነበር። በዚሁ ጽሁፋቸው “የትግራይ ተወላጆች ያለ ሀጥያታቸው ፍርድ ቤት ሳያውቃቸው ከያሉበት እየታፈሱ እየታሰሩ ነው” ያሉት አቶ አብርሐ የተፈቱትም ቢሆኑ የንግድ ሥራዎቻቸው በመዘጋታቸው፤ “ለፍተው ያጠራቀሙትን የገዛ ገንዘባቸው አውጥተው እንዳይጠቀሙ የባንክ አካውንታቸው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ” በመታገዱ ችግር ላይ እንደሚገኙ ጽፈው ነበር።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የአቶ አብርሐ ጠበቃ ደንበኛቸው ትናንት ቅዳሜ በቀረቡበት ፍርድ ቤት ለተጨማሪ ዘጠኝ ቀናት በእስር እንዲቆዩ መወሰኑን እንደተናገሩ ሬውተርስ ዘግቧል። የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብርሐ አሁን ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ውጊያ የገጠመው ህወሓት ያቋቋመው ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሳለ ለ3 አመታት ታስረዋል። አቶ አብርሐ ደስታ በኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት በተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። (ምንጭ መረጃ)