የህወሓት ታጣቂዎች በዳባት ወረዳ በጭና በፈጸመው ጭፍጨፋ ከ200 በላይ ንጹሀን ተገድለዋል። ከእነዚህ ንጹሀን መካከል የወይዘሮ ካሳዬ ዘውዱ ባለቤት አንዱ ናቸው። “ባለቤቴን ቤታችን በር ላይ ያለምንም ጥፋቱ በግፍ ገደሉት። አስከሬኑን መቅበር ባለመቻሌ በቤቴ ውስጥ ይዤ ለሶስት ቀናት ቆይቻለሁ” ሲሉ ባለቤታቸው በግፍ የተገደሉባቸው ወይዘሮ ካሳዬ ዘውዱ በሥፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ተናግረዋል።
ወይዘሮዋ ዛሬም ድረስ ባልወጣላቸው ሀዘን ውስጥ ሆነው፤ በጭና በግፍ የተገደሉ በርካታ ንጹሃንን በወጉ መሰረት መቅበር የተቻለው ወራሪው ቡድን ከአካባቢው ተሸንፎ እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ መሆኑን ነግረውናል። በርካቶችም ሞተው ከወደቁበት ተነስተው የተቀበሩት ከሳምንት በኋላ ነው ብለዋል።
ዘጠኝ ቤተሰብ ያላቸው ወይዘሮ ካሳዬን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ወራሪው ቡድን በፈጸመው ጥቃት ቤታቸው ፈርሷል፤ ንብረታቸው ተዘርፎም ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል። (ኢ.ፕ.ድ)