ከሦስት ሳምንታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በዋስ የተለቀቀችው የ“ኢትዮ ንቃት” የማኅበራዊ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራ የቀረበባት ክስ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ ነው አለች።
ለሁለተኛ ጊዜ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. በፖሊስ ተይዛ በእስር ላይ የቆየችው መስከረም አበራ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ዓ.ም. አንቀጽ 14ን በመተላለፍ በዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባት ከጠበቆቿ መካከል አንዱ የሆኑት ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም፣ የአሁኑ እስር ያልጠበቀችው እና “ዱብዕዳ” እንደሆነባት ለቢቢሲ ተናግራለች።
የጨቅላ ልጅ እናት የሆነችው መስከረም ክሱ በመጀመሪያ ላይ ከሽብር ጋር የተያያዘ እንደነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዘ ወንጀል መሆኑን እንደተነገራት ገልጻ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ጽሁፏን በድምጽ ያቀረበው ግለሰብ ከእሷ ጋር መከሰሱን መስማቷ የበለጠ ግራ አጋብቷታል።
ጠበቃዋ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ በዝርዝር እንዳስረዱት ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ መስከረም በሥራዋ በሕዝብ ደኅንነት ላይ ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ፤ ጥላቻን፣ አመጽን፣ ሁከትን እና ግጭትን በማሰብ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን በብሔር ለመከፋፈል እና አገር ለማፍረስ ማሰብ የሚል እንደሆነ አመለክተዋል። (ምንጭ ቢቢሲ)