የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ከትግራይ አለመመለሳቸው አሳስቦኛል – የሰላም ሚኒስቴር

ወደ ትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው የገቡ ከባድ ተሽከርካሪዎች በተቀመጠው የአሰራር ስርዓት መሰረት ተመልሰው መውጣት ሲገባቸው አለመመለሳቸው አሳስቦኛል ሲል የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጨባጭ ከዓላማቸው ውጭ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም ብሏል፡፡

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ነባራዊ ሁኔታውን በተገቢው በመገንዘብ በአሸባሪው ቡድኑ ምክንያት እየተስተጓጓለ ያለው የእርዳታ ስርጭት ለዜጎች በአግባቡ እንዲደርስ ተገቢውን ጫና ማሳረፍ እንደሚገባ ሰላም ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

በእስካሁኑ ሂደት ትናንት እና ዛሬ የተንቀሳቀሱትን 152 መኪኖች ጨምሮ በድምሩ 500 ገደማ መኪኖች የግብርና ግብዓቶችን (ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ) ፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዘዋል፡፡

ይሁን እንጂ በጥፋት ቡድኑ በተደጋጋሚ በአፋር እና አማራ ክልል በተካሄደው ወረራ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት እንዲሁም የእርዳታ መተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ በሚያደርስው ጉዳት እርዳታ የማድረስ ሂደቱን ውስብስብ አድርጎታል ብሏል፡፡

ቀደም ሲል ከመነሻው እስከ መድረሻው የነበሩ ሰባት የፍተሻ ጣቢያዎችን ወደ ሁለት የፍተሻ ጣቢያ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በአሸባሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ በአፋር እና አማራ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለጉዳት የተዳረጉ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ (ምንጭ- ኢዜአ)