በትግራይ ክልል የኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ

በትግራይ ክልል ያሉ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ ድጋፍ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ ለኤርትራውያን ስደተኞች ጥበቃ እንዲያደርጉ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያ ጥሪ አቀረቡ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ ተጠሪ በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖች በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች በተመለከተ በርካታ ተአማኒ ክሶች መቀበላቸውን ተናግረዋል።

በኤርትራ ስላለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የድርጅቱ ተጠሪ የሆኑት ዶክተር ማሐመድ አብዲልሳላም ባቢኬር እንዳሉት “በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች፣ በኤርትራ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች አማካይነት ስለተፈጸሙ ከፍ ያሉ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ እርዳታ ሕግጋት ጥሰቶች ተአማኒ ክሶችን” ተቀብለዋል።

“ኤርትራውያን ስደተኞች ተነጥለው በግጭቱ ተሳታፊ ከሆነው ከአንደኛው ወገን ጋር ይተባበራሉ ተብለው በሁሉም ኃይሎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል” ብለዋል።

የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ዩኤንኤችሲአር እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች መግቢያ አጥተው በተለያዩ ካምፖች ያሉ ሲሆን የረድኤት ድርጅቶችም ድጋፍ ሊያደርጉላቸው አልቻሉም።

በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች በመዛመቱ በትግራይና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 80 ሺህ ያህል ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በችግር ላይ ይገኛሉ። ሙሉ ዘገባውን ቢቢሲ ላይ ያንብቡ።