ጠ/ሚሩ ከጀነራሎች ጋር መከሩ

የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ የተደረገው ውይይት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበና አለምአቀፋዊ ዝማኔን መሰረት ያደረገ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሰክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ፡፡የኢፌዲሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለመከላከያ ሠራዊት ጀነራል መኮንኖች የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ይህንኑ በማስመልከት የጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሰክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተቋሙ ህግና ስርዓትን የሚያስጠብቅ እንደመሆኑ ዘላቂነት ባለው መልኩ ለየትኛውም አካል ሳይወግን ገለልተኛ ሁኖ እንዲያገለግል የሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂ መነደፉን ገልጸዋል።

ስትራቴጂው የተቀረጸው ከዚህ ቀደም የነበረውን መመሪያ ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ ለማዘመን ታስቦ እንደ አዲስ ሁሉም የሰራዊት አባላትን የሚያቅፍና ዘላቂ ለሀገር ግንባታ በሚውል መልኩ በተዋረድ ይወያዩበታልም ብለዋል፡፡

ህዝቡም የመከላከያ ሰራዊት የሚገነባበትን መንገድ ማወቅ ስላለበት በሂደት ስትራቴጂው ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት። ከዚህ ቀደም የነበረው የመከላከያ ሰራዊት በህብረ ብሄራዊነት ላይ እንከን የሚታይበት እንደነበርም አስታውሰዋል።