የትግራይ ክልል ምርጫ ህጋዊ አይደለም – ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ

ህወሐት መንግሥት የሥራ ዘመኑን በማራዘም ምርጫ ለማካሄድ ያቀረበውን አማራጭ በመቃውም፤ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ “የክልሉ መንግሥትም ሆነ ክልሉን ሚያስተዳድረው ፓርቲ ምርጫ ማካሄድ ሕጋዊ አይሆንም” ሲሉ ለኢቢሲ ተናግረዋል።

ህወሐት ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማካሄድ ስለመወሰኑ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለማሳወቁን ወ/ት ብርቱኳን “ለኛ ፎርማሊ የደረሰን ነገር” የለም በማለት አስረድተዋል።

“ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ አስበው ከሆነ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም። ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንም” ያሉት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ እርሳቸው የሚመሩት ብቸኛው ምርጫ ቦርድ መሆኑን በማስታወስ፤ “በፌደራል፣ በክልል እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የማስፈጸም ስልጣን የተሰጠው ለምርጫ ቦርድ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ውጪ የክልል መንግሥታትም ሆኑ የፌደራል አስፈጻሚ አካል ተስቶ ምርጫን በተመለከተ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንምም ብለዋል።

ወ/ት ብርቱኳን ከአጠቃላይ ምርጫ በተለየ ጊዜ የአንድ አካባቢ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል ግን ጠቁመዋል። እንደ ምሳሌም፤ ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል አብዛኛው ድምጽ ሰጪ በኑሮ ዘያቸው ምክያት በድምጽ መስጫ አካባቢ የማይገኙበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ በማስታወስ ከአጠቃላይ ምርጫ በኋላ በክልሉ ምርጫ እንደተከናወነ አስታውሰዋል።

መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም ምርጫውን ማካሄድ ያስችላሉ ያላቸውን አራት አማራጮች ማቅረቡ ይታወሳል። ከቀረቡት አማራጮች መካከል ደግሞ ዛሬ ረፋድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ሚለውን አማራጭ አጽድቋል።