ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሚካኤል መላኩ በፍርድ ቤት፦ «ተጠርጥረውበታል የተባሉት ወንጀሎች በኢትዮጵያ ሕግም ኾነ በሌላ መልኩ ወንጀሎች አይደሉም» ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ አጥኚ አቶ ፍስሐ ተክሌ ዛሬ ተናገሩ።
ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሚካኤል መላኩ በፍርድ ቤት፦ «ተጠርጥረውበታል የተባሉት ወንጀሎች በኢትዮጵያ ሕግም ኾነ በሌላ መልኩ ወንጀሎች አይደሉም» ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ አጥኚ አቶ ፍስሐ ተክሌ ዛሬ ተናገሩ። ሁለቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለመታሰራቸው ምክንያት የኾነው ጉዳይ እንዳውም፦ «በዓለም አቀፍ ሕግ የተሰጣቸውን መብት እየተጠቀሙ እንደነበር ነው የሚያሳየው» ብለዋል። «እነዚህ ሰዎች መታሰርም አልነበረባቸውም፤ ስለዚህ ነው በአፋጣኝ እና ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲለቀቁ ያልነው» ሲሉ አቶ ፍስሐ አክለዋል። ሄኖክ እና ሚካኤልንም «የኅሊና እስረኞች ልንላቸው የምንችላቸው ሰዎች ናቸው»ም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሰሙት ንግግርን በማጣቀስም፦ «ፖሊስ አቅም ስለሌለው ብዙኃን ታስረው ሊኾን ይችላል ብለው፣ የእኛንም የመብት ጥሰት እንዳለ የነበረንን ጥርጣሬ አረጋግጠውልናል» ሲሉ አክለዋል አቶ ፍስሐ። የሲቪክ መጫወቻ ሜዳው ሊሰፋ ይችል እንደነበር በበርካቶች ዘንድ ተጠብቆ የነበረ እንደኾነ የገለጡት የአፍሪቃ ቀንድ አጥኚው፦ «አሁን የምናየው ነገር፤ በመቃወማቸው፤ አኹን ደግሞ የአዲስ አበባን ሕዝብ እናደራጃለን፣ ለመብቱ እንዲቆም እናደርጋለን ብለው የተነሱ ሰዎች መታሰራቸው ወደኋላ የሚመልስ ነገር ነው» ብለዋል። ድርጊቱንም «አሳሳቢ» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። «ከመስከረም ወዲህ የመንግሥት አካላት ቀጥታ የመብት ጥሰት ውስጥ መግባት ጀምረዋል» ያሉት አቶ ፍስሐ ኹኔታው፦«የተገባውን ቃል የሚያፈርስ ነገር ነው። ተስፋችን ላይ ውኃ የሚቸልስ ነገር ነው። እነዚህ ነገሮች መስተካከል አለባቸው። «መንግሥት በተለያየ ጊዜ፤ በተለያየ ቦታ ላይ የሰዎች መብትን የሚጥሱ አካላት ላይ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ነው መጀመር ያለበት እንጂ ከመንግሥት አቋም የተለየ ሐሳብ ያንጸባረቁ ወይንም መንግሥት ያልወደደውን ሐሳብ ያንጸባረቁ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ ችግሩን አይፈታውም» ብለዋል።