በጨለንቆ ከአንድ ቤተሰብ አምስት ሰው ተገደለ

በጨለንቆ ባለፈው ሰኞ በሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ቢያንስ 16 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶችም ቆስለዋል። ከተገደሉት ሰዎች አምስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ሳሊ ሃሰን ኢብሮና አብዲ ሳሊ አባትና ልጅ ናቸው ። ሚካኤል አብዲ ሃሰንና ቶፊቅ አብዲ ሃሰን ደግሞ የሳሊ ሃሰን ኢብሮ የወንድማቸው ልጆች ነበሩ ፤ ሌላኛው ሟች አብደላ ኢሳምም ቢሆን የቅርብ ዘመዳቸው ነው።

አዲ ሃሰንና ቶፊቅ አሊ በሃያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ሚካኤል አብዲ ደግሞ የ15 ዓመታ ታዳጊ ነበር።
ሳሊ ሃሰንና አብደላ ሊሳ ደግሞ የ50 እና የ60 ዓመት አዛውንቶች እንደነበሩ ነው የቤተሰቡ አባል የሆነው አብዱልሰላም አባድር ሃሰን ለቢቢሲ የተናገረው ።በወቅቱ እኚህ የአንድ ቤተሰብ አባላት ከጨለንቆ ከተማ በ6 ኪሜ ርቀት አካባቢ በሚገኘው ኢጀኤራ በተባለ ስፍራ በደቦ ማሽላ ሲሰበስቡ እንደነበር ይገልፃል።

” ጦሩ ሲመጣ መንገድ ሲዘጉ የነበሩት ልጆች ተደዋውለው ሸሹ፤ በዚህ ጊዜ ነበር በአካባቢው ሰብል ሲሰበስቡ የነበሩት ባሉበት የተገደሉት።” ሟቾቹ ስለነበረው ተቃውሞ ሆነ በከተማዋ ስለነበረው ነገር ረብሻ መረጃ እናዳልነበራቸው ይናገራል። “የመኖሪያ ቤታቸውና የእርሻ ቦታቸው ይራራቃል፤ ሰብል ለመሰብሰብ የሄዱ ሰዎች ይኖሩ ይሆን ብለን ስንሄድ እዛው በተመቱበት ወድቀው ነው ያገኘናቸው” ይላል። በቀብሩ ዕለትም ቢሆን ችግር እንደነበር ይናገራል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጨለንቆ ከተማ ግድያውን የፈጸመው ከኦሮሞ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እውቅና ውጪ እንደሆነ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ለኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ(ኦ ቢ ኤን) በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።ግድያውንም አጥብቀው እንደሚቃወሙና ወንጀሉን የፈጸሙትን አካላት ህግ ፊት ለማቅረብ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
የግድያው መነሻ በሜታ ወረዳ ሰርከም በተባለው ቦታ የሶማሌ ልዮዩ ፖሊስ አንድ ሰው መግደሉን ተከትሎ የተከሰተ የህዝብ ተቃውሞ ነው።በዚሁ ቀን አምስት ቤተሰቦቹ እንደወጡ የቀሩበት አብዱልሰላም ስለጉዳዩ ማንን እንደሚጠይቁም ገራ መጋባቱን ይገልጻል።“ለምን እንደተገደሉ የገለጸልንም ሆነ መጥቶ ያናገረን አካል የለም ፤ ወዴት ነው አቤት የምንለው? ያለን አማራጭ እርስ በእራሳችን እየተዛዘንን ፈጣሪን መለመን ብቻ ነው” ብሏል::