የጎንደርና የባህርዳር ዮኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አደረጉ

ከሰኞ ዕለት ጀምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲካሄድ የቆየው የተማሪዎች ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ በዛሬው ዕለት በተለይ በጎንደር እና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደረግ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡:በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ ወደ ግቢው የዘለቁት የታጠቁ ወታደሮች፣ በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸው ታውቋል:: ወታደሮቹ ወደ ግቢው መግባታቸውን ተከትሎ፣ ተማሪዎች በጩኸት ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር የገለጹት እማኞች፣ ወታደሮቹ ቁጥራቸው ያልታወቀ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እማኞቹ አክለው ገልጸዋል:: በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ የተነሳ፣ ካለፉት ሶስት ቀናት ወዲህ የትምህርት አገልግሎት መስጠት ያቆመው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ዛሬም ትምህርት ተቋርጦበት ውሏል:: በተመሳሳይ ሁኔታም፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ትምህርት ለመጀመር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በግልጽ ተናግረዋል- እንደ መረጃዎች ገለጻ:: ተማሪዎቹ፣ በትግራይ ክልል አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ ሳሉ፣ በክልሉ ተወላጆች ጥቃት ተፈጽሞባቸው የተገደሉ ወንድሞቻችን አስከሬን ተጠቃሎ ይመለስ የሚል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ ጥቃት ይፈጸምብናል ብለው በስጋት ላይ የሚገኙ እህት እና ወንድሞቻችንም ወደየቤተሰቦቻቸው ይመለሱ ሲሉ ጠይቀዋል:: አለበለዚያ ግን በተቃውሟቸው እንደሚገፉበት አሳስበዋል