ኢ/ር ስመኘው ስለ ግድቡ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ዝግጅት ላይ ነበር

ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን በወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በትዕግስትና በጽናት በጋራ እየፈታን ለውጡን ልናስቀጥል ይገባል!
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈት የተነሳ የኢፌዴሪ መንግሥት እና ህዝብ በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ይገኛሉ። የኢፌዴሪ መንግሥት በእኚህ ታላቅ የልማት አርበኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በድጋሚ እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ይመኛል።

የእኚህ ታላቅ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ህልፈት የተሰማው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ደረጃ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳወቅ ጋዜጠኞችን በአካል ቦታው ድረስ ወስደው በተጨባጭ ለማሳየት በዝግጅት ላይ እያሉ ነበር።

ስለአሟሟታቸው ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ የተጠናከረ የወንጀል ምርመራ በመካሄድ ላይ ሲሆን ምርመራው ተጠናቆ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እስኪሆን ድረስ መላው ኢትዮጵያውያን በትዕግስት እንዲጠባበቁ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

በአሁኑ ጊዜ አገራችን የተያያዘችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ እያስገኘልን ያለውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ ወዳጅም ጠላትም በአንድ ቃል የሚመሰክሩት ነው። በመሆኑም ይህንኑ ለውጥ አጠናክሮ መቀጠል ይገባናል።

የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ጉዞ በማንኛውም ጊዜ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት እንደሚችል መገንዘብ የሚገባ ሲሆን አንዳች ፈተና ባጋጠመን ቁጥር በስሜታዊነት የምንወስዳቸው እርምጃዎች ዞረው የለውጡን ጥልቀትና ስፋት እንዳይገድቡ እና እንዳያደናቅፉት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ፣ በትዕግስትና በጽናት እየተቋቋምን ከያዝነው ዓላማ ዝንፍ ሳንል በጋራ እየፈታን ማለፍ ይገባናል።

በመሆኑም እጅግ ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ብዙሃኑ ህዝባችን የሚፈልገውን ለውጥ በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል ነገሮችን በእርጋታና በትዕግስት እያስተናገድን፣ ችግሮችን በህጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በጋራ እየፈታን ለውጡን ለማስቀጠል እንድንረባረብ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታና የሠላም ችግሮችንም መላው ህዝባችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ ሠላም ወዳድነት መንፈስ በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ግንባር ቀደም ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በተለይም የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶቻችን ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ የአገር ፍቅር ስሜትን፣ ስራ ወዳድነትን እና ጽናትን በመውረስ እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ለውጥ ለስኬት ለማብቃት በእልህ እና በቁጭት እንዲነሳሱ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።
መላው ህዝባችንም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የተለመደውን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁጭት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል።

በተጨማሪም፣ መላው ኢትዮጵያውያን የታላቁ አገር ወዳድ፣ የልማት አርበኛ ኢንጂነር ስመኘው በቀለን አርዓያነት በመከተል በየተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ የየራሳችንን አሻራ በማስቀመጥ የተሻለች አገር ለመፍጠር እየተካሄደ ያለውን ጥረት በማገዝ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈን እንድንረባረብ ጥሪውን ያቀርባል።

ሀምሌ 20 ቀን 20010 ዓ.ም.