የመንግስት ባለስልጣናት ቪ8 ተሽከርካሪዎችን ከተማ ውስጥ እንዳይጠቀሙ ተከለከለ

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የሌሎች ተቋማት ሀላፊዎች ቪ8 ተሽከርካሪዎችን ከተማ ውስጥ እንዳይጠቀሙ የሚከለክለው መመሪያ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

መመሪያው ባለስልጣናቱ እና የስራ ሀላፊዎቹ ከዚህ ቀደም በከተማ እንቅስቃሴ ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቪ8 ተሽከርካሪዎችን ለመስክ ስራ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚደነግግ መሆኑንም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ በሰጡት መግለጫ፥ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ሀምሌ 28 2009 ዓ.ም በካሄደው 38ኛ መደበኛ ስብሰባ ለፌደራል መንግስትና ሌሎች ተቋማት ሀላፊዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት ስርአት እንዲኖር መመሪያ ማውጣቱ አስታውሰዋል።

በመመሪያው መሰረትም ኮሚቴ በማቋቋም የተግባራዊነት ጥናት እና ጨረታ በማውጣት የተሽከርካሪ ግዢ ሲካሄድ መቆየቱን አቶ ሐጂ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊው ስራ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ሐጂ፥ በቀጣይ ሳምንት ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።

በዚህም መሰረት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የፍደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች ባለ 8 ሲሊንደር ቪ8፣ ጂ ናይን ወይም ባለ 4 ሲሊንደር ፕራዶ ፓጃሮ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ የሚፈቀደው ለመስክ ስራ ብቻ ይሆናል።

ባለስልጣናቱ እና ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች በከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ደግሞ በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ ዲ ኤፍ ኤም ኤስ ሀምሳ አውቶሞቢሎችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል።

የአንድ ቪ8 ተሽከርካሪ ዋጋ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሲሆን፥ የአንድ ባለ 2ሺ ሲ.ሲ አውቶሞቢል ዋጋ ደግሞ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ነው።

የነዳጅ ፍጆታን በተመለከተም ቪ8 ተሽከርካሪ በ1 ሊትር ነዳጅ 7 ኪሎ ሜትር ብቻ በሚጓዝ ሲሆን፥ በአውቶሞቢል ግን በ1 ሊትር ነዳጅ 13 ኪሎ ሜትሮችን ማሽከርከር ያስችላል ብሏል ሚኒስቴሩ።

አዲሱ መመሪያ ከወጪ ቅነሳ አንጻር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አቶ ሐጂ ኢብሳ ተናግረዋል።

(ምንጭ.- ኤፍ.ቢ.ሲ)