(በቁምላቸው ደርሶ) ጾታዊ ፍቅር ውስጥ በብዛት ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ዋናው እንዴት እንደሚወደኝ እና ወደፊት አብሮኝ እንደሚዘልቅ እርግጠኛ እሆናለሁ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ በፊት እወድሃለሁ አንተን ብቻ ነው ማግባት የምፈልገው ብላህ አሁን ከሌላ ሰው ጋር ህይወቷን እየቀጠለች ያለችው የቀደሞ የፍቅር አጋርህ ትዝ አለችህ ? እወድሻለሁ ያላንቺ ህይወቴ ባዶ ነው ብሎሽ ወሲብ ከፈጸማችሁ በኋላ አይንሽ ላፈር ያለሽስ? በቅርቡ አንድ ወዳጄ ወንድ ልጅ ሲወድ/ሲያፈቅር በምን ያስታውቃል ብላ ጠየቀችኝ፤ እርግጥ ነው ይህ ጥያቄ የብዙዎቻችን እንደሚሆን አልጠራጠርም ሁሉም ሰው የእራሱ የሆነ የማፍቀር እና ፍቅሩን/መውደዱን የመግለጪያ መንገድ ቢኖረውም ብዙዎቻችንን ሊያስማሙ የሚችሉ መልሶችን እስኪ አብረን እንያቸው፡፡
1. ያስተዋውቅሻል
ወንድ ከወደደሽ እና ካፈቀረሽ በሄደበት ቦታ ሁሉ ተመሳሳይ ወሬ ከተነሳለት ስላንቺ የሆነ ነገር ያወራል፡፡ ከጓደኞቹ ወይም ከቤተሰቦቹ ጋር ያስተዋውቅሻል አልፎ አልፎም አንድ ላይ እንድታሳልፉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ አንቺም አብረሽው ለመታየት አና አብራችሁ በምታደርጉት ነገር በአብሮነታችሁ በአጠቃላይ አታፍሪም፡፡
2. ይንከባከብሻል/ለደስታሽ ይጨነቃል
ደስታን ያስገኙልሻል ብሎ የሚያስባቸውን ነገሮች ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይንከባከብሻል፡፡ ጠንካራ ሰራተኛ ቢሆንም በስራው ቅድሚያ ግን ላንቺ ነው የሚሰጥሽ፡፡ በችግርሽም ሆነ በደስታሽ ጊዜ ቀድመው ከሚደርሱልሽ ሰዎች መካከልም አንዱ ነው፡፡
3. ኮከብህ ከኮከቡዋ ይገጥማል
መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማለትም ስለወደፊት እቅዳችሁ ስታስቡ ተመሳሳይነት ይታይበታል ለምሳሌ ስለ ትዳር ስለ ልጅ የሚኖርህ እቅድ እሷም ከሚኖራት ጋር ይመሳሰላል፡፡ እዚህ ጋር ግን ልብ የምትልልኝ ነገር መሰረታዊ የሚባሉት ነገሮች ላይ ትኩረት እንድትሰጥ ነው፡፡ ወደፊት ካንተ ጋር ተጣምራ ለመኖር ስታስብም ሰርጉ ሳይሆን ይበልጥ የሚያስደስታት ወደፊት ከአንተ ጋር የምታሳልፋቸው ጊዜያቶች ናቸው፡፡
4. እንደ እራስህ አድርጋ ትቀበልሃለች
በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከሚፈጠሩ ችግሮች መካከል ዋነኛው የፍቅር አጋርን አኛ እንደምንፈልገው ቀርጸን ነው እንጂ እሱ እንደሆነው አይደለም የምንቀበለው፡፡ ስዚህ ወዳጄ የምትወድህ ከሆነ አንደሆንከው አድርጋ ትቀበልሃለች፡፡
5. የረጅም ርቀት ፍቅር ያሳለፋቹ እንደሆነ
ለብዙዎቻችን ፍቅር በርቀት እንደ ጦር የሚፈራና አይሳኩልንም ብለን ከምናስባቸው ተግባራት መካከል የሚመደብ ነው፤ ሆኖም ግን ፍቅራችሁ በረጅም ርቀት ውስጥ ተፈትኖ ያለፈ እንደሆነ አብራችሁ እስከ መጨረሻው የምትዘልቁበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ጥናቶች እና የአንዳንድ ጥንዶች ተሞክሮዎች ያመለክታሉ፡፡
6. ሁሌም ያበረታታሻል
በጥረትሽ እና በሙከራሽ ውስጥ የሚያበረታታሽ ሲሆን እንዲሁም እንድታሳኪም አልፎም የተሻለች አንቺ እንድትሆኚ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከሆነ ይህ ሰው ባል የሚሆን ወንድ ነው ማለት ነው፡፡
7. አብረሃት ስትሆን ራስህን መሆን ከቻልክ
ብዙ ወንዶች የምንወዳት ሴትን ለመማረክ እሷ እንደምትወደው ዓይነት ወንድ ሆኖ ለመገኘት እንጥራለን፡፡ ሆኖም ግን ቅሉ ያለው ከርሷ ጋር ስትሆን ራስህን መሆን ከቻልክ ነው፡፡ አብሮነቷ አንተነትህን እንድትቀይር የማያስገድድህ ከሆነ ወንድሜ ይህቺ ሴት ሚስትህ ለመሆን እጅግ በጣም ቅርብ ናት፡፡