መፅሐፍ አንብቦ ያልተለወጠ ሠው ካላነበበው ሠው ምንም የሚለየውና የሚሻለው ነገር የለም

(እ.ብ.ይ.)

ወዳጄ ሆይ…. መፅሐፍት የሚያስተምሩህ በሠውነትህ ላይ ሌላ ሠዋዊ ተፈጥሮ እንድትጨምር ሳይሆን ትክክለኛ፣ ዓላማ ያለው፣ ዕውቀት ያለው፣ ምግባርና ንግግሩ አንድ የሆነና መልካም ማንነት ያለው ሠው መሆን እንዴት እንደምትችል ነው፡፡፡

መፅሐፍት ዓላማና ራዕይ እንዲኖርህ የዕውቀት ስንቅ ያዘጋጁልሃል፡፡ ለራስህና ለዓለም በጎ ታሪክ ጥለህ ማለፍ እንድትችል ብርታትና ጥንካሬ፣ መልካም አመለካከትና ቅንነት እንዲኖርህ ያግዙሃል፡፡ ይሄ የሚሆነው ግን ጎበዝ ተማሪ ከሆንክ ብቻ ነው፡፡ ጎበዝ ተማሪ መሆን ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ የተማረውን በተግባር መሞከር የሚችል ብልህ የተግባር ሠው መሆንም ይጠበቅብሃል፡፡

መፅሐፍ አንብቦ ያልተለወጠ ሠው ካላነበበው ሠው ምንም የሚለየውና የሚሻለው ነገር የለም፡፡ እንደው ለወሬ ፍጆታ ብቻ ካልሆነ በስተቀር! መፅሐፍት ዓለምን እንደቴሌቪዥን ያሳዩሃል፡፡ ዓለም ውስጥ ገብተህ በዕውቀት እንድትንቦራጨቅና የጥበብ ባህሩ ላይ መዋኘት እንደትችል አማካሪህ ሆነው ያገለግሉሃል፡፡ ነገር ግን እንደአንተ አይተውኑልህም፡፡ ተዋኙ ወይ ተዋንያኑ አንተው ራስህ ነህ፡፡ ተውኔቱ ደግሞ ሕይወትህ ነው፡፡ መቼቱ ኑሮህ ነው፡፡ መድረኩ ዓለምህ ነው፡፡

ያነበብከውን በአዕምሮህ አመላልሠህ፣ ሃሳብ ጨምረህና ተንትነህ መሬት አውርደህ በተግባር አስመስክረህ የምትኖርበት አንተ ነህ፡፡ ካንተ ሌላ ላንተ ማንም አይመጣም፡፡ መፅሐፍት መነሳሳት፣ እውቀትና ክህሎት እንዲኖርህ ከጀርባ ሆነው ይገፉሃል፡፡ መንገዱን የምትጀምረው ግን አንተው ራስህ ነው፡፡ ያላንተ ያንተን መንገድ የሚሄድ ማንም የለም፡፡

በዙሪያህ ያሉ ሠዎች ልክ እንደመፃሕፍቱ ለዓላማህ እንድትቆም ይመክሩህ፣ ይዘክሩህ፣ ያነሳሱህ ይሆናል እንጂ መንገድህን አይራመዱልህም፡፡ ሠው’ነትህ ላይ በጎ ምግባርና መልካም ዕውቀት እንድትጨምር መፅሐፍት ይረዱሃል እንጂ ራሳቸው ወደውስጥህ አይገቡም፡፡ ጨማሪውም ሆነ አስገቢው አንተው ራስህ ነህ፡፡ በምንነትህ ላይ ማንነትህን እንድትገነባ የመጽሐፍት ገፆቹ እንደመስታወት ሆነው ዓለሙን ያሳዩሃል፡፡

አንባቢ ሁሉ ባነበበው አይታነፅም፡፡ ብልህ አንባቢም መሆን ይጠበቅብሃል፡፡ ትንሽ አንብበህ ብዙ ማሠላሠል ግድ ይልሃል፡፡ ያነበብካቸውን ቁምነገሮች ከራስህ ሃሳብ ጋር እያስተሳሰርክና እያዋሃድክ የራስህ አዲስ ሃሳብ እንዲኖርህ መፅሐፍት መንገዱን ይጠርጉልሃል፡፡ የሁሉም ነገር ቁልፍ ያለው አንተው እጅ ላይ ነው፡፡ ቁልፉ ደግሞ አስተሳሰብህ ነው፡፡ የቁልፉ ጋን ምግባርና ተግባርህ ነው፡፡ ያነበብከውን በተግባር ካላረጋገጥክ መረጃ እንጂ ዕውቀት አልያዝክም ማለት ነው፡፡ ዕውቀት ማለት በማንበብ የሠበሰብከውን መረጃን በመጠቀም ለበጎ ዓላማ በተግባር በስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ ዕውቀት በተግባር የሚገለፅ እንጂ በወሬ ላይ ብቻ የተንጠላጠለ አይደለም፡፡ ተማሪ የሚማረው ሊሠራበት ነውና ያነበብከውን አመዛዝነህ፣ ከራስህ ሃሳብ ጋር አዛምደህ፣ ከዘመኑ አዋጅተህ፣ የራስህን ሃሳብ ፈጥረህና አሳድገህ በገቢር ታውለው ዘንድ በርታ፡፡

መፅሐፍት ጌጥ ሳይሆን የነፍሳችን ምግብ ነው፡፡ ምግቡን አላምጦና አጣጥሞ መዋጥ ግድ ይላል፡፡ መዋጫ ውሃው አመለካከት ነው፡፡ አመለካከትህ መልካም ካልሆነ ጣፋጩ እሬት ይሆንብሃል፡፡

ወዳጄ መፅሐፍት ውስጥ የምታገኛቸውን ቁምነገሮች እንደ ማስቲካ አላምጠህ ከመትፋት ይልቅ አጣጥመህ ዋጣቸው፡፡ ማጣጣም ማለት ከራስ ሃሳብ ጋር ማስታረቅ ነው፡፡ ማጣጣም ማለት በሌሎች ሃሳብ ምሣሌነት የራስን ሃሳብ ማግኘት ነው፡፡ የሌሎችን ሃሳብ እንዳለ መገልበጥ ሳይሆን የራስን ሃሳብ በሌሎች መስታወትነት መስራት ነው፡፡ አበቃሁ!

ቸር ጊዜ!

_______________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሐሙስ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.