በሳውዲ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሰቆቃ

ከቡታጅራ ከተማ ተነስታ ከአራት ዓመት በፊት በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ያቀናችው ለይላ አወል፣ ከአስከፊው የአራት ወራት የሳዑዲ እስር ቤት ቆይታ በኋላ፣ ረዕቡ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ በአንድ እጇ ቋጠሮዋን የሸከፈችበትን የላስቲክ ከረጢት በሌላኛው ደግሞ የሦስት ዓመት ልጇን ይዛ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ከአውሮፕላን ስትወርድ፣ የረገጠችውን መሬት እየሳመች ከማልቀስ በስተቀር ያሳለፈችውን ሰቆቃ የሚገልጽ ድርጊት አልነበራትም፡፡ አዲስ አበባ ስትደርስ በሚኒስትሮችና ሌሎች ባለሥልጣናት የተደረገላትን አቀባበል ልብ ያለችውም አይመስልም፡፡

‹‹ኤምባሲው አንድም ቀን ዞር ብሎ ዓይቶን አያውቅም፡፡ በሪያድ ያለውን የእኛ ኤምባሲ ከመጠበቅ ጭራሽኑ የሉም ብሎ መቀመጥ ይቀላል፤›› ስትል ያሳለፈችውን ጭንቀትና ሰቆቋ ተናግራለች፡፡

ለይላ እንዲሁ እዚህ ዓይነት ምሬት ላይ አልደረሰችም በላስቲክ ከያዘችው ልብስ ጋር ወደ አገር ቤት ይዛው የመጣችው ልጇ አንድ ወር ሙሉ እስር ቤት ውስጥ ታሞ ሕክምና አላገኘም፡፡ ሕክምና ለማግኘት የታሰሩበትን ክፍል በር ሲያንኳኩ ጠባቂዎች ይሰጧቸው የነበረው ምላሽ ‹‹ሰው ሲሞት ብቻ ነው የምታንኳኩት›› የሚል እንደነበር ከመከራው ወጥታ አዲስ አበባ ከገባች በኋላም አላባራ ያለውን እንባዋን እያፈሰሰች ትናገራለች፡፡

‹‹በሳምንት አንዴ ወይም ደስ ያላቸው ቀን የታመመ አለ ወይ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሰው በድንገት ታሞ ትንፋሽ ቢያጥረው ግን ይሙት አያገባንም አታንኳኩብን ነው የሚሉት፤›› በማለት የከረሙበትን ሁኔታ ታስረዳለች፡፡ ሙሉ ታሪኩን ሪፓርተር ላይ ያንብቡ