ኢሰመጉ መንግሥት በሳዑዲ እስር ቤት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተገቢ ትኩረት እንዳልተሰጠው ገለጸ

ከአንድ ዓመት በላይ በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች በሕገወጥ መንገድ እስርና ጥቃት እየተፈጸመባቸው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መንግሥት የሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ፡፡

ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ በሳዑዲ ዓረቢያ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የዘመቻ እስር እየተደረገባቸው ነው፡፡ የዘመቻ እስሩን ተከትሎ ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤቶች ውስጥ ኢሰብዓዊ አያያዝ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ከተለያዩ የሚዲያ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል ያለው ኢሰመጉ፣ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማቆም በሚል በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በተጀመረው ዘመቻ ሕጋዊ ኢትዮጵያውያን ጭምር የዘመቻ እስሩ ሰለባ ሆነዋል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ማሰቃየት፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ ድብደባ፣ የምግብና የሕክምና ክልከላ ሰብዓዊ ክብርን የሚጋፋ አያያዝ እንደሆነ በመግለጫው ያመላከተው ኢሰመጉ፣ በአንድ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ክፍሉ ሊይዘው ከሚችለው በላይ በርካታ የሆኑ እስረኞች ታስረው እንደሚገኙ፣ የእስር ቤት ክፍሎቹ ንፅህናቸው ያልተጠበቀ በመሆኑ ለበሽታ እየተጋለጡ እንደሆነና በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ በሕይወት ያሉትም ብዙዎቹ በሕመምና ያለ ምንም ሕክምና እንደሚገኙ አስታውቋል ሲል ሪፓርተር ጋዜጣ ዘግቧል።