ህወሃት ህጻናትን ለጦርነት እየማገደ ነው

ህወሃት ህፃናትን ወደ ጦር ሜዳ እየማገደ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን ጠበቃና የህግ ባለሙያ ዳዊት መንግስቱ ተናግሩ።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2000 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላለ ጉባኤ በፀደቀው የህፃናት መብት ኮንቬሽን ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎትት መጠቀም እንደማይቻል ይደነግጋል።

ኮንቬሽኑ ከ2002 አመት ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ተደርጎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተግበራዊ እየተደረገ መሆኑን የህግ ባለሙያው ዳዊት መንግስቱ ይገልፃሉ።

ይሁን እንጂ አሸባሪው የህውሃት ቡድን ዓለም አቀፉን የህፃናት መብት ኮንቬሽን በመፃረር ህፃናትን ለጦርነት እየዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ህፃናትን አደንዛዥ እፅ እንዲጠቀሙ በማድረግ ለውጊያ እያሰለፈ ከባድ ወንጀል በመፈፀም ላይ ነው ብለዋል።

ህፃናትን በትምህርት እና በእውቀት አጎልብቶ የነገ አገር ተረካቢ ማድረግ ሲገባ የህወሃት አሸባሪ ቡድን በትግራይ ትውልዱ እንዳይቀጥል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የአሸባሪውን ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች በዝምታ ከማለፉ ይልቅ ሊያወግዙ ይገባል ብለዋል።

የህፃናት ህክምና እና እንክብካቤ ስፔሻሊስት ዶክተር ሄኖክ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ህፃናትን ከቤተሰባቸውና ከትምህርት ገበታቸው ነጥሉ ወደ ጦር ግንባር እንዲገቡ ማድረግ ለአካላዊ ለስነ ልቦናዊ ችግሮች እንዲጋለጡ ያደርጋል ብለዋል።

በተለይ ህፃናት ማህበረሰቡን በሚቀላቀሉበት ወቅት ከማህበረሰብ መገለል፣ ለድህረ አደጋ ጭንቀት፣ ጥላቻ፣ ሌሎችን ለማጥቃት መነሳሳት እና ለመሳሰሉ ችግሮች ይዳረጋሉ ሲሉ አስረድተዋል።

ህፃናቱን በጦር ሜዳ እንዲሳተፉ ያደረጉ አካላት በጦር ወንጀል መጠየቅ አለባቸው ያሉት ዶክተር ሄኖክ አጥፊዎቹ እንዲጠየቁም የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።

የህወሃት አሸባሪ ሃይል በውስጥና በውጭ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከሚሰሩ አካላት ጋር የጥፋት ግንባር በመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል።