ገደቡ ካልተነሳ የበጀት ድጎማውን እንደማይለቅ የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ

የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ እስካልተፈቀደ ድረስ፣ ለኢትዮጵያ ያፀደቀው የበጀት ድጎማ እንደማይለቀቅ አስታወቀ።

የኅብረቱ ምክትል ኮሚሽነርና የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ  ጆሴፍ ቦሬል በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ቀውስ መባባስ የአውሮፓ ኅብረትን በእጅጉ እንደሚያሳስበው፣ በዚህ ጉዳይ ላይም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በውይይታቸው ወቅትም በትግራይ ክልል ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ኅብረቱን እንደሚያሳስበው ለአቶ ደመቀ እንደገለጹላቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለ ምንም ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ሊፈቀድ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ዓርብ ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቀዋል።

‹‹ይህ የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገ የመንግሥታት ግዴታ ነው፤›› ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አመልክተዋል።