አቶ ልደቱ አያሌው ከ 4 ወር እስር በኋላ በዋስ ተፈቱ

በኦሮሚኛ ቋንቋ ድምፃዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት፣ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ከተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የታሰሩት አቶ ልደቱ አያሌው ከ140 ቀናት እስር በኋላ ታኅሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በ30,000 ብር ዋስ ተፈቱ፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ፣ ለእስር የተዳረጉት ፖሊስ ተከታትሎ ፈልጎ አግኝቷቸው ሳይሆን፣ ከፌዴራል ፖሊስ ስልክ ተደውሎላቸው እንደሚፈለጉ ሲነገራቸው፣ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ከሄዱ በኋላ፣ በወንጀል መጠርጠራቸው ተነግሯቸው መሆኑን በወቅቱ መግጻቸው ይታወሳል፡፡

የቢሾፍቱ ወጣቶች ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ሁከትና ብጥብጥ የፈጠሩት አቶ ልደቱ ገንዘብ ስለከፈሏቸው መሆኑን መረጃ እንደደረሰውና በወንጀል እንደጠረጠራቸው ገልጾ ለፌዴራል ፖሊስ በማሳወቁ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወስዶ እንዳስረከባቸውም መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ፣ ፖሊስ ምርመራውን መጨረሱን ለፍርድ ቤት ሲያሳውቅ፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቻ ጊዜ ሳይጠይቅ ወይም በምርመራው ክስ እንደማይመሠረትባቸው ሳይናገር በዝምታ በማለፉ፣ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪውን በሚመለከት ትዕዛዝ ሳይሰጥ መዝገቡን በመዝጋቱ በወቅቱ ቅሬታዎች መነሳታቸውም ተዘግቧል፡፡ አቶ ልደቱ በፖሊስ ጣቢያ የተሰወሰኑ ቀናቶች ከቆዩ በኋላ ማመልከቻ በመጻፍ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ወይም በነፃ እንዲያሰናብታቸው ሲጠይቁ፣ ዓቃቤ ሕግ የፀና ፈቃድ ሳይኖር ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱን የመረመረው በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አቶ ልደቱ በመቶ ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

በትዕዘዛዙ ቅር የተሰኘው የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አፅድቆታል፡፡ አቶ ልደቱ ሁለቱም ፍርድ ቤቶች በዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ቢሰጡም ለቀናት ሳይለቀቁ ቆይተው፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥዊ ሥርዓቱን ለመናድ በማሰብ ‹‹የሽግግር መንግሥት ማቋቋም›› የሚል ሰንድ በማዘጋጀትና ሕዝብ ለረብሻና ለብጥብጥ የሚያነሳሳ፣ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› የሚል መጣጥፍ ማዘጋጀት ወንጀል የሚል ሌላ ሁለተኛ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ክሱን የመረመረው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት፣ ክሱን ከመረመረ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡