የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮችን በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠ

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ፤ ለተጠርጣሪዎች ተፈቅዶ በነበረው ዋስትና ላይ ፖሊስ የመልስ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 19 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ዋጃና ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የተጠርጣሪዎችን አቆያየት በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ከሰዓት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም በጠዋት ችሎት ቀርበው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች አልተገኙም በሚል ብይኑን ለዛሬ ማሳደሩን ጠበቃው ገልጸዋል። እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲጠብቁ የቆዩ ሰባት ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐዋሳ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጋቸውንም አክለዋል።

ዛሬ ረፋዱን በነበረው ችሎት በህመም ምክንያት ትላንት ከሰዓት ያልተገኙት ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር ተብሏል። ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎም ከዛሬ ችሎት መጠናቀቅ በኋላ ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች በፖሊስ መኪና መወሰዳቸውን የስድስት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተመስገን ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።