የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት እስከ መጪው ሐሙስ ድረስ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በመግባት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጀምር ተነገረ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና ከህወሓት ሪዎች ጋር የተደረገውን ድርድር መንግሥትን በመወከል በመሪነት የተሳተፉት አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን እንዳሉት ሠራዊቱ በዚህ ሳምንት ወደ መቀለ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ለሁለተኛ ጊዜ ናይሮቢ ላይ በተደረሰው መግባባት መሠረትም የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ መሳሪያዎቻቸውን የማስረከቡ ተግባር እንደሚጀመርም ሬድዋን ገልጸዋል።
ሰኞ ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም. ከአንድ ዓመት ተኩል ከሚሆን ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ የተመራ የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑካን ቡድን መቀለ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ነው አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚጠበቁ ቀጣይ ጉዳዮችን ያመለከቱት። ( ምንጭ ቢቢሲ)