ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከታዩት የህትመት ሚዲያዎች መካከል ከፍ ያለ ተነባቢነት እና ዝናን አትርፋ የነበረችው የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ባልደረቦች ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ታምራት ነገራ ዳግም ለስደት ተዳርጓል።
ታምራት ነገራ እና የአዲስ ነገር ባልደረቦች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይመራ ከነበረው መንግሥት በገጠማቸው ጫናና ስጋት ከአገር ተሰደው ለዓመታት መቆየታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ባካሄዱት ለውጦች ተበረታተው ወደ አገር ቤት ከተመለሱት የጋዜጣዋ ባልደረቦች መካከል ታምራት ነገራ አንዱ ነው።
ለዓመታት ከቆየባት አሜሪካ የተመለሰው ታምራት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመስጠት እና በመንግሥት ላይ ጠንካራ ትችቶችን በመሰንዘር ይታወቃል።
ኋላ ላይም “ተራራ ኔትወርክ” የተባለውን የራሱን የዩቲዩብ ቻናል በመጀመር ዜና እና ትንታኔዎችን ሲያርብ ቆይቷል። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ መጀመሪያ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ከቤቱ ተወስዶ ለአራት ወራት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ በዋስ መፈታቱ ይታወሳል።
ታምራት መጋቢት ወር ማብቂያ ላይ ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ሥራው ሳይመለስ ለወራት ድምጹ ሳይሰማ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ከባለቤቱ ጋር ዳግም ወደ ስደት ተመልሷል።