የኢትዮጵያ መንግሰት የኢንተርኔት አፈናውን አጠናክሮ መቀጠሉን ፍሪደም ሀውስ አስታወቀ

በኢትዮጵያ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የሚፈጸመው አፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ፍሪደም ሀውስ የተሰኘው ዓለም ዓቀፍ የሰው ልጆች መብት ተከራካሪ ቡድን አስታወቀ፡፡ መንግስት በሀገር ውስጥ ሆን ብሎ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንደሚያቋርጥ ያስታወቀው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፣ በተለይ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ የሚደረገው ጸረ መንግስት ተቃውሞ በሚደረግበት ወቅት መሆኑንም ደርጅቱ ይገልጻል፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የኢንተርኔት ነጻነት ከሌለባቸው ሀገራት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ዓለም ዓቀፉ የመብት ተከራካሪ ተቋም ፍሪደም ሀውስ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሰኔ 2016 እስከ ግንቦት 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ኩነቶችን በዳሰሰበት የሪፖርቱ ክፍል፣ በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ከቀን ወደ ቀን ወደ አዘቅት እያመራ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በቻይና ብቻ ተበልጣ ሁለተኛዋ የኢንተርኔት አገልግሎት ጨቋኝ ሆና ተፈርጃለች፡፡ በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው ከኢንተርኔት አገልግሎት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሞባይል ስልክ ኔትዎርክ ችግር አለ፡፡ በተለይ በተቃውሞ ወቅቶች ሆን ተብሎ የስልክ ኔትዎርክ እንዲጠፋ እንደሚደረግም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ተማሪዎች ለፈተና በሚቀመጡበት ጊዜም ማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚከረቸም የድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ሪፖርቱ ትንታኔው ይቀጥልና፣ ባለፈው ዓመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ራስን በራስ ሳንሱር የማድረግ አዝማሚያ መፈጠሩንም ይጠቁማል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሀሳባቸውን የገለጹ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች እና ጋዜጠኞች ወህኒ መወርወራቸውን ያስታወሰው የፍሪደም ሀውስ ሪፖርት፣ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የዓመታት ፍርድ እንደተላለፈባቸውም ይጠቁማል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት አማካይነት እየተፈጸመ ያለው የኢንተርኔት እና የስልክ አፈና ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው እና ‹‹የሚታለብ ላም›› እየተባለ በመንግስት የሚገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በስልክ እና በኢንተርኔት ጠለፋ ላይ እንደሚሰማራ ይታወቃል፡፡ በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን እና ጋዜጠኞችን ስልክ እና ኢንተርኔት በመጥለፍ ስለላ የሚፈጽመው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከዚህ ቀደም ከህወሓት የደህንነተ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን እና ለመንግስት አስጊ የሚባሉ ሰዎችን ስልክ እና ኢሜይል መጥለፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡