በዓለም ላይ በፖሊስ አማካይነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጸምባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ተገለጸ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ምርምር ሲያደርግ የሰነበተው አንድ ዓለም ዓቀፍ ተቋም፣ በ2016 በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከፖሊስ ጋር ተያይዞ በተከናወኑ ጉዳዮች ላይ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱን ያካሔደው የፖሊስ ሳይንስ ጥናት ማህበር የተባለ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ሲሆን፣ ጥናቱም የኢኮኖሚ እና ሰላም ማኅበር ከተባለ ሌላ ተቋም ጋር በጋራ መካሔዱ ታውቋል፡፡
በጥናቱ ላይ እንደተገለጸው፣ ጥናቱ የተካሔደው በ127 የዓለም ሀገራት ላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ደረጃ 115 ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ይህ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ የፖሊስ ሰራዊትን በመጠቀም ምን ያህል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ እንደሚገኝ አመላካች ሆኗል፡፡ ጥናቱ እንዳወጣው ደረጃ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ፖሊሶች በዜጎቻቸው ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከሚያካሂዱ የዓለም ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ በጥናቱ ላይ አስከፊ ጥቃት እንደሚፈጽሙ የተነገረላቸው የናይጄሪያ ፖሊሶች ሲሆኑ፣ በደረጃም የመጨረሻው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል-127ኛ ላይ፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ እንደ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ቦትስዋና፣ አልጄሪያ ጋና፣ ቡርኪናፋሶ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ፖሊሶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጽሙ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዎቹ ሆነው ተቀምጠዋል-ኢትዮጵያን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጎረቤት ሀገር ኬንያ እና ዩጋንዳ በፖሊስ በኩል ከፍተኛ ግፍ ከሚፈጸምባቸዋው ሀገራት መካከል ተቀምጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፖሊስ አደረጃጀት፣ ከህዝብ ይልቅ ለገዥው ቡድን የወገነ እና ግደል ሲባል የሚገድል፣ ደብድብ ሲባል የሚደበድብ መሆኑ በተለያየ ጊዜ ተረጋግጧል፡፡ ህዝብ መብቱን ለመጠየቅ ሰልፍ በወጣባቸው የተለያዩ ወቅቶች፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዱላን ጨምሮ፣ ጥይት እና መሰል አጥቂ ቁሶችን ተጠቅሞ ሰልፍ ሲበትን ኖሯል፡፡ በሰልፈኞች ላይ ጥይት መጠቀም አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለ ድርጊት መሆኑ ይታወቃል፡፡