(በሰብለወንጌል አይናለም) የፍቅር ህይወት በተሞክሮ ውስጥ የምናልፍበትና በሂደት የምናዳብረው ክህሎት ነው፡፡ እንደ ሰው በፍቅር ግንኙነት ውስጥ መፈጸም የማይገባንና የፍቅር አጋራችንን ስሜት ሊጎዱ የሚችሉ ስህተቶችን ልንፈጽም እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡ የጓደኛችንን የልደት ቀን መርሳት፡ በቀጠሮ ሰዓት መዘግየት፡ የፍቅር ጓደኛችንን የስጦታ ምርጫ አለማወቅና የመሳሰሉት ለጊዜው ቅሬታ ቢፈጥሩም፤ ተወቃቅሰንና ተነጋግረን በይቅርታ ልናልፋቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የፍቅር ግኑኝነታችን ጤናማ ሆኖ እንዳይቀጥል የሚያደርጉና ቀጣይነቱን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱን ስህተቶችም ይኖራሉ፡፡ የሚከተሉት አምስት ስህተቶች በፍቅር ግንኙነት ላይ አዳጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ፡፡
- ምልዑነትን መጠበቅ (Expecting Perfection):- ብዙዎቻችን ወደ ፍቅር ግንኙነት የምንገባው ፍቅረኛችን ውብ እንደሆነ/ች እና በሁሉም ነገር ደግሞ ብቁ እንደሆኑ አድርገን አስበን ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ውስጥ የፍቅር አጋራችን ጉደለቶች መታየት ሲጀምሩ ያንን ሰው አስበነው ወደ ነበረው ምልዑነት ለመቀየር ግርግር መፍጠር እንጀምራለን፡፡ ሰዎች ደግሞ በባህሪያቸው በማንነታቸው እንዳሉ ተቀባይነት እንዲያገኙ እንጂ “የመቀየር አለብህ/አለብሽ ” ግፊት ብዙም ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ ለዚህ መፍትሄው የፍቅር አጋርዎን አሁን ባለበት ሁኔታ ሳያቅማሙ መቀበል፤ ሁሉም ሰው (እራስዎን ጨምሮ) ጉድለቶች እንዳሉበት መረዳትና የፍቅረኛችንን ክፍተቶች እኛ መሙላት የምንችልበት መንገድ ካለ መሞከር የተሻለ ነው፡፡
- መወስለት (Cheating)፡- ፍቅር በመርህ ደረጃ የሁለት ተቀራኒ ፆታዎች የአካልና የመንፈስ ውህደትን ይጠይቃል፡፡ ከፍቅረኛችን አሻግረን ሌላ ይምናይ ከሆነ፤ ይባስ ብሎም ከሌላ ተቃራኒ ፆታ ጋር የስሜት ትስስር መፍጠር ወይም ወሲብ መፈጸም የፍቅር ግንኙነትን በፍጥነት ከሚገድሉ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስህተት ውስጥ የገቡ ከሆነ ማድረግ የሚገባዎት የፈጸሙትን ስህተት ለፍቅረኛዎ ነግሮ፤ በቀጣይ መደረግ ስለሚገባው ጉዳይ መወያየት ነው፡፡ ውስልትናን ከፍቅር ጓደኛ ደብቆ ማቆየት ቢቻልም በግንኙነታችን ላይ ተጽዕኖውን በተለያየ መንገድ ስለሚያሳርፍ ፍቅራችንን ይገድለዋል፡፡
- ማኩረፍ (Silent treatment):- በፍቅር ግንኙነት ውስጥ አለመግባባቶችና ጸቦች ይከሰታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮችን ለመፍታት የምንመርጠው መንገድ ማኩረፍ፤ ስልክ መዝጋትና መሸሽ ከሆነ የፍቅር ግንኙነታችን እየገደልነው ነው፡፡ ፍቅርን ጠብቀው ከሚያቆዩ ምሰሶዎች አንዱ ግልጽ ውይይት ነው፡፡ ንዴታችን እስኪበርድልን ጠብቀን በአልተግባባንበት ጉዳይ ላይ መነጋገር ወደተሻለ መንገድ ይመራናል፡፡ በተቃራኒው ያልተወያየንባቸው አለመግባባቶች በውስጣችን በተጠራቀሙ ቁጥር፤ ግንኙነታችን በየጊዜው ይረበሻል፡፡
- ውሸት (Lying):-የፍቅር ግንኙነትን ጤናማነት ጠብቀው ከሚያቆዩ ነገሮች አንዱ ሀቀኝነት ነው፡፡ ማንኛውንም ጉዳይ ለፍቅረኛችን/ የትዳር አጋራችን በግልጽ የመናገር ልምድ ሲኖረን ግንኙነታችን ይጠነክራል፡፡ ነገር ግን ጓደኛችን በሆነ ጉዳይ ላይ ስንዋሽ ከያዘን/ከያዘችን በቀጣይ ለመታመን ዋስትና የለንም፡፡ ለምሳሌ፡- ስራ ቦታ አምሽቼ ወደ ቤት እየገባሁ ነው ያሉት አፍቃሪዎ ከሌሎች ጓደኞችዎ ጋር ካፌ ውስጥ ሲዝናኑ እንደነበር ቢያውቅ በሌላ ቀን ስራ ቦታ ቢያመሹ እንኳን የፍቅረኛዎን እምነት ማግኘት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን እውነቱን ብቻ የመነጋገር ልምድን ማካበት ይኖርብናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር የመወያየት ባህል ቢኖረን ግንኙነታችን ይጠነክራል፡፡ ከፍቅር አጋራችን ደብቀን የምንይዛቸው ጉዳዮች ካሉ በጊዜ ሂደት ግንኙነታችንን ሊያሻክሩ ይችላሉ፡፡
- ቂም መቋጠር (Holding a grudge):- ማንም ሰው ከስህተት የጸዳ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት የተሰሩ ስህተቶችንና ይቅርታ የተጠየቀባቸውን ጉዳዮች ሁልጊዜ እንደ አዲስ እያነሱ ፍቅረኛን መውቀስ፤ አንቺኮ ከዚህ በፊትም እንዲህ አድርገሽኛል፤ አንተኮ ባለፈውም እንዲህ በድለኸኛል እየተባባልን የምንነታረክ ከሆነ ፍቅራችንን ውሃ እያስበላነው ነው፡፡ ከቂምና በቀል ያልጸዳ ግንኙነት መሰረቱ ጽኑ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ያለፉ ስህተቶቸን በይቅርታ መርሳት፤ ወደፊት ደግመው እንዳይከሰቱ ደግሞ መፍትሄ መቀየስ ያሻል፡፡
መልካም የፍቅር ጊዜ!!!