“ፊቴ ላይ ነው ልቡን ረግጠው የገደሉት፣ የእስር ቤቱ ኃላፊ እያለ ነው የተደበደብነው”
“ሁላችንም ዋስትና የለንም። በሚቀጥለው የእኔን የሞት ዜና ልትሰሙ ትችላላችሁ”
“ሳትፈርዱብን ገድለው ይጨርሱናል” 1ኛ ተከሳሽ ብስራት አበራ
(በጌታቸው ሺፈራው)
በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት “በእስር ላይ እያሉ በአድማ ስምምነት በማድረግ በሰዎችና ንብረት ላይ የሀይል ድርጊት በመፈፀም ከማረሚያ ቤቱ ለማምለጥ የእስረኞች አመፅ ውስጥ ተሳትፈዋል” በሚል ክስ የቀረበባቸው ሁለት ተከሳሾች በድብደባ ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ የአይን እማኞች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ገልፀዋል።
በእነ ብስራት ብርሃኑ ክስ መዝገብ 15ኛ ተከሳሽ አለማዬ ዋቄ ማሞ ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ ተደብድቦ መገደሉን 1ኛ ተከሳሽ ብስራት ብርሃኑ የአይን አማኝነቱን ገልፆአል። ከአለማዬ በተጨማሪ መሃመድ ጫኔ ገበየሁ የተባለ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦበት የነበረ እስረኛም በድብደባ ህይወቱ እንዳለፈ እስረኞቹ ዛሬ ጥቅምት 15/2010 ዓም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
1ኛ ተከሳሽ ብስራት አበራ ” አይኔ እያየ ፊቴ ላይ ነው ልቡን ረግጥ የገደሉት። ሁላችንም ተደብድበናል። የእስር ቤቱ ኃላፊ ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳነ እያለ ነው የተደበደብነው” ሲል እማኝነቱን ለፍርድ ቤት ሰጥቷል። ሟች አለማዬ ዋቄ ከአሁን ቀደምም በተደጋጋሚ ለችሎቱ መደብደቡን በመግለፅ አቤቱታ ማቅረቡን እስረኞቹ ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል። የጳውሎስ ሚሊኒዬም ሆስፒታል የአለማዬ ዋቄን አሟሟት የሚገልፅ 6 ገፅ የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤቱ የላከ ሲሆን የምርመራ ውጤቱ “እንደማንኛውም ሰው ኢንፌክሽን ነበረበት” ከማለቱ ውጭ ቀሪው የምርመራ ውጤት ምን እንደሚል ፍርድ ቤቱ አልገለፀም።
ሟች አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር እና በዛሬው ዕለት መሃል ዳኞ ሆነው በችሎቱ የተቀመጡት ዳኛ አቤቱታውን ሰምተው እንደነበር እስረኞቹ ለችሎቱ አስታውሰዋል። 1ኛ ተከሳሽ “ባለፈው ፍርድ ቤት ከዚህ ማረሚያ ቤት አስወጡኝ። ይገድሉኛል ብሎ ተናግሮ ነበር። ሁላችንም አደጋ ላይ ነን። የት እንሂድ? ገዳዮች እጅ ነው ያለነው። እኔ ተመልሼ ወደ ቂሊንጦ አልሄድም። ይገድሉኛል። እዚሁ በጥይት ይግደሉኝ ” ሲል ስጋቱን በመግለፅ ከችሎት አልወጣም ብሏል። 1ኛ ተከሳሽ ብስራት አበራ ሁሉም እስር ቤቶች ስቃይ የሚፈፀምባቸው ቢሆኑም ለህይወቱ ሲል ከቂሊንጦ ወደ ማዕከላዊም ወይም ወደ ቃሊቲ ቢዛወር እንደሚመርጥ ለፍርድ ቤቱ ቢያስረዳም ፍርድ ቤቱ ከቂሊንጦ ወደ ሌላ እስር ቤት እንዲቀየር ትዕዛዝ እንደማይሰጥ ገልፆአል።
ሌሎች ተከሳሾች ከችሎት ሲወጡ አንደኛ ተከሳሽ “ዛሬም የተናገርኩት በህይወቴ ፈርጄ ነው። ጓደኞቼን እንደገደሏቸው ይገድሉኛል። አልሄድም” ብሎ ችሎት ውስጥ የቆየ ሲሆን ፍርድ ቤቱ “ምንም ልናደርግ አንችልም” ስላለው ከቆይታ በኋላ ከችሎት ወጥቷል። ሆኖም ችሎቱ በር ላይ ፖሊሶች እጁን ከሚገባው በላይ አጥብቀው በማሰር ስለዛቱበት ወደችሎቱ ተመልሶ በመግባት እጁን ለፍርድ ቤት አሳይቷል። እንደዛቱበት እና ያቀረበው አቤቱታ ተጨባጭ ስለመመሆኑ ችሎቱ በር ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ዋቢ አደርጎ ቢያስረዳም ፍርድ ቤቱ ላቀረበው አቤቱታ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል። ከችሎት ውጭ ለነበረው ህዝብ እየተፈፀመበት ያለውን በደል፣ ህይወቱ አደጋ ላይ መሆኑን ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲናገር ተስተውሏል።
በእነ ብስራት አበራ የክስ መዝገብ ስር ያሉት ተከሳሾች በዚህ ክስ ለምርመራ ሸዋ ሮቢት ተወስደው ስቃይ እንደደረሰባቸው፣ ቂሊንጦ እስር ቤትም ተመሳሳይ በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ነበር። ፍርድ ቤቱም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ባዘዘው መሰረት ኮሚሽኑ ቂሊንጦ ሄዶ እስረኞቹን ቢያነጋግርም ምርመራውን ሳያቀርብ ቀርቷል። ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑን የምርመራ ውጤት ለመስማት በተደጋጋሚ ቀጠሮ ቢይዝም ኮሚሽኑ ምርመራውን አለማቅረቡን ገልፆ ለህዳር 4/2010 ምርመራውን ለምን እንዳላቀረበ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ከአለማዬ ዋቆ በተጨማሪ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦበት የነበረ መሃመድ ጫኔ ገበየሁ የተባለ ሌላ ተከሳሽም በድብደባ ህይወቱ እንዳለፈ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። “ከአሁን ቀደምም መሃመድ ጫኔን ገድለዋል። አሁን አለማየሁን ገድለዋል። ሁላችንም ዋስትና የለንም” ያለው አንደኛ ተከሳሽ ” በዚህ አይነት ከዚሁ ሁሉ እስረኛ አንድ እስረኛ ላይ እንኳ አትፈርዱም። ቀድመው ገድለው ይጨርሱናል። በሚቀጥለው ቀጠሮ ደግሞ የእኔን የሞት ዜና ልትሰሙ ትችላላችሁ” ሲል ያለባቸውን ስጋት ገልፆአል።
አየለ በየነ፣ መሃመድ ጫኔ እና አለማዬ ዋቄ ባለፈው አራት ወር እስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው ያለፈ እስረኞች ሲሆኑ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችም ድብደባ እንደሚፈፀምባቸው እና ለህይወታቸው እንደሚሰጉ እየገለፁ ይገኛሉ። አግባው ሰጠኝ፣ ዘመነ ጌቴና ለነሰ ወልደሃና በተደጋጋሚ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ለህይወታቸውም እንደሚሰጉ መገለፁ ይታወሳል