በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰማሩ ወታደሮች እንዲወጡላቸው ተማሪዎች ጠየቁ

በጥበቃ ሰበብ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰማሩ የተደረጉ ወታደሮች ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡላቸው ተማሪዎች ጠየቁ፡፡ ጥያቄው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚማሩ ተማሪዎች መቅረብ ከጀመረ ቆየት ቢልም፤ እስካሁን ግን ምላሽ ሊያገኝ እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎም ጥያቄው ዳግም እየተነሳ እንደሚገኝ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ወታደሮች በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በብዛት መሰማራት የጀመሩት ተማሪዎች ያስነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ ሲሆን፤ ወታደሮቹም ተቃውሞ ባሰሙ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ በተወሰደው የኃይል እርምጃም በርካታ ተማሪዎች ድብደባ፣ ማዋከብ እና ማንገላታት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የሞተ ተማሪ እንደሚገኝም ከዚህ ቀደም ይፋ የሆኑ የመረጃ ምንጮች ጠቁመው ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት ለማብረድ በሚል ሰበብ የተሰማሩት ወታደሮች ራሳቸው የውጥረት ምንጭ ሆነው መገኘታቸውን ከተማሪዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ወታደሮቹ ቀንም ሆነ ማታ ግቢ ውስጥ መዋላቸውን ያልወደዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ የይውጡልን ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ሰሚ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁን ሰዓት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ተቋርጦ የሚገኝ ሲሆን፤ በከፊል ትምህርት በሚሰጥባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ወታደሮች መሰማራታቸውን ከዓይን እማኞች ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ትምህርት በተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም ቢሆን፤ ወታደሮች ተሰማርተው እንደሚገኙ እማኞቹ ይናገራሉ፡፡ በወታደሮች ተከብቦ መማር ነጻነት ይነፍጋል የሚሉት ተማሪዎቹ፤ ወታደሮች ከተሰማሩ በኋላ እንደ ልብ ከግቢ መውጣትም ሆነ በፈለጉት ሰዓት ወደ ግቢ መግባት እንደተከለከለም ተናግረዋል፡፡ እንደ መረጃዎች ገለጻ፤ በአሁን ወቅት የጸጥታ አካላት ከተሰማሩባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባምንጭ፣ ሀረማያ፣ ወልድያ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ፡፡