በደምቢዶሎ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ

በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ክልል ደምቢዶሎ ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ፡፡ በሰልፉ ላይ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይም በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን አገዛዝ የሚያወግዙ የተቃውሞ ድምጾች ሲሰሙ ውለዋል፡፡ በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ፣ በጨለንቆ እና በሌሎች የኦሮሚያ ክፍሎች የተገደሉ ንጹኃን ዜጎች ታስበው የዋሉ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታም በምዕራብ ሐረርጌ በኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ለሞቱ ሰዎች የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ተካሂዷል

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ተገኝቶ ተቃውሞው ሲያሰማ መዋሉን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አስረድተዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ከመመኘት በተጨማሪም፣ የተለያዩ መፈክሮች ሲደመጡ ተስተውለዋል፡፡ የህወሓት አስተዳደር ስልጣን እንዲለቅ የጠየቁት የሰልፉ ተካፋዮች፣ በዚህ ስርዓት መተዳደር እንደሰለቻቸውም በግልጽ ተናግረዋል፡፡

በጨለንቆ፣ በአምቦ እና በሌሎችም የኦሮሚያ ክፍሎች፣ ንጹኃንን በመግደል እጃቸው ያለበት ወታደሮች እንዲሁም ግድያው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጡ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑም የደምቢዶሎ ከተማ ሰልፈኞች ጠይቀዋል፡፡ የንጹኃን ደም፣ ደመ ከልብ ሆኖ እንዳይቀር የጠየቁት ሰልፈኞቹ፣ ወንጀለኞች የእጃቸውን ማግኘት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገው ጸረ ህወሓት ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም በሌላኛው የኦሮሚያ ክፍል መቱ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ በትላንትናው ዕለት አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረው የመቱ ከተማ ህዝብ፣ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ተቃውሞዉን ቀጥሎ ውሏል፡፡ በዚህ የተቃውሞ ትዕይንተ ህዝብ ላይ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በብዛት የተገኙ ሲሆን፣ ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም በሰልፉ ላይ ተገኝቶ የህወሓት አገዛዝ እንዲያከትም ጠይቋል፡፡