በሚኤሶ ጥቃት የተፈጸመባቸው ጋዜጠኞች ሾፌር አቶ ሱሌይማን አህመድ ሕይወት አለፈ

ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ በነበረ የድሬዳዋ ከተማ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኞች ቡድን አባላት ላይ በተፈጸመ ድብደባ የቡድኑ ሾፌር አቶ ሱሌይማን አህመድ ከቀናት የሕክምና ክትትል በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተደረገውን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አቀባበል ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ አዲስ አበባ እየመጣ በነበረበት ወቅት ሚኤሶ ከተማ ላይ ሲደርሱ በተሰባሰቡ ወጣቶች የቡድኑ አባላት ጥቃት ደርሶባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች፣ ‹‹እናንተ (በተለይም ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚችሉትን ጋዜጠኞች) ገንዘብ ተከፍሏችሁ እየሰለላችሁ ነው፤›› በሚል ሁሉንም የቡድኑ አባላት የጅምላ ጥቃት እንዳደረሱባቸውም ይታወሳል፡፡

በድብደባው ጭንቅላታቸውና ጎናቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት አቶ ሱሌይማን፣ በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታልና በሐረር ከተማ ሕይወት ፋና ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ ቢደረግላቸውም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም፡፡

አቶ ሱሌይማን ወደ አዲስ አበባ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመላክ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በቤተሰቦቻቸው ጥያቄ ወደ ሐረር መላካቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የድሬዳዋ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሐሰን ኢጌ፣ በመጨረሻ ሐሙስ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. 5፡00 ሰዓት አካባቢ ሕይወታቸው ሊያርፍ ችሏል ብለዋል፡፡

ጋዜጠኞቹ ላይ በደረሰው ጥቃት እስካሁን የፖሊስ ምርመራ አለመጀመሩንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የ37 ዓመቱ አቶ ሱሌይማን የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ከነፍሰጡር ሚስታቸው አራተኛ ልጅ ይጠብቁ ነበር፡፡ አቶ ሱሌይማን በኤጀንሲው ከአምስት ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡

(ምንጭ፡- ቢቢሲ፣ ዘጋቢ ዳዊት እንደሻው)