የብአዴን ክፍተቶች – ክፍል አንድ – በአንሙት አብርሃም

(በአንሙት አብርሃም) ክፍል አንድ

#ብዐዴንን_ብሔራዊ_ጥያቄ_አልወለደውም:- የዛሬው ብዐዴን የቀድሞው ኢህዴን ከአፈጣጠሩ ህብረብሔራዊ ጥያቄንና አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚል ትግል የጀመሩ ወጣቶች የመሰረቱት እንጂ ሊመልሰው የተነሳው ብሔራዊ ጥያቄ አልነበረም:: መስራቾቹም ብሔራዊ ትግል አገር አፍራሽ ነው የሚል እምነት የነበረው ኢህአፓ አባላት የነበሩ ናቸው :: ብሔራዊ ጥያቄን አንስተው ብሔራዊና አገራዊ ምላሽ መስጠት ይቻላል የሚል እምነት ይዘው ሳይሆን በህብረብሔራዊ ትግል ብሔራዊ ጥያቄዎች ይመለሳሉ በሚል እስከድል ዋዜማ የቀጠሉ ናቸው::
የትግል አጋራቸው ህወሓት የትግሉ ምክንያት ብሔራዊ ጭቆና ነው አማራጩም ብሔራዊ ትግል ነው በሚል ፅኑ እምነት የታገለ ነው::

የትግሉን አመክንዮ ከመተንተን አልፎ ብሔራዊ መሰረቱ የሆነውን የትግራይ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ምንነት (ጥንካሬና ጉድለት፣ ፀጋና ፈተና) Define አድርጎ: ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንደሚፈልግ ተንትኖ የተነሳ ነው:: የወቅቱ የትግል አጋሩ ኢህዴን ግን ስለኢትዮጵያ አጠቃላይ ችግሮች እንጂ የተለያዩ ህዝቦችን ዝርዝር ብሔራዊ የጥያቄ መሰረቶችንና ፍላጎቶችን የለየ ነበር ለማለት ያስቸግራል:: ከድል በኳላም የታገለላቸው ዓላማዎች ከህብረብሔራዊነት ይልቅ ወደ ብሔራዊ ይዘት ተለውጠውበት አዲስ ማንነት መያዙን ማየት ይቻላል::

ኢህዴን ወደ ብዐዴን ሲለወጥም አስራ ምናምን ዓመት የደከመለት ህብረብሔራዊ አጀንዳ ቢያንስ የቅርፅ ለውጥ ሲያመጣና አዲስ ማንነት ሲይዝ እየዘመረና ግጥም እየገጠመ ፍቅሩን ይገልፅላት የነበረችው ኢህዴን የውሃ ሽታ ስትሆን የድርጅት ፍቅርና ታማኝነት አብረው ሲመንኑ ጓዳዊ ፍቅርን ይዘው ወደ አዲሱ ማንነት ቀጠሉ:: በዚህ የስያሜና የመደብ ሽግግር ቀላል የማይባሉ ታጋዮች ደስተኛ አልነበሩም:: ህወሓት ደግሞ ብሔራዊ የትግል አጀንዳውን ለአጋሩ ኢህዴን ብቻ ሳይሆን ለአዲስ መጭዎቹ ኦህዴድና ደኢህዴንም አጋርቶ ቀጠለ::
እናም ኢህዴን/ብዐዴን የአማራ ህዝብ ብሔራዊ ማንነት፣ ጥያቄና ፍላጎት ምንድን ነው የሚለውን define ባላደረገበት አዲስ ማህበራዊ መሰረት ለመያዝ ትግል ጀመረ:: አማራ ማን ነው? የሚለውን ሳይመልስ መሰረቴ ነው ቢልም በብሔሩ ልሒቃን እየተፈተነ ቀጠለ:: ፍላጎትን በጥቅል የልማትና ዲሞክራሲ ሽፋን መመለስ ዳገት ሆኖ አለ::

ባልተተነተነ ብሔራዊ ጥያቄና ፍላጎት እየተፈተነ ቀጥሎ: ዛሬ ላይ ብሔራዊ ጥያቄን ካነገቡ አባላትና ህዝብ ጋር መላተም ጀምሯል:: define
ባልተደረገ ብሔራዊ ፍላጎት (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ፣…) የአማራ ብሔርተኝነት አዲስ መሰረት እየያዘ ነው::
(ይቀጥላል)