ስለ አማራ ~ ፋኖ ይሂድ አትከልክለው!!

(በየትነበርክ ታደለ)

…”ሀገሪቱ” የምትተዳደረው በብሄር ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስት ተሸክማ ነው። ስለዚህም ማንኛውም ሰው ራሱን “በሀገሪቱ” ፖለቲካ ውስጥ ለማግኘት ከፈለገ፣ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል ከፈለገ፣ ራሱን በተቀመጠው የፖለቲካ ውድድር ውስጥ ተሻምቶ ቀዳሚ ሆኖ ለመገኘት ከፈለገ……የግድ የግድ የግድ በብሄር መደራጀት አለበት።

….በዚህ ረገድ ላለፉት 27 አመታት በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው የተጠቀሙ ብሄሮች እንዳሉ ሁሉ ዳር ዳሩን በልዝብ ሲጓዝ የተጎዳም ብሄር አለ። የተጠቀሙት እሰየው እንኳን ተጠቀሙ። ማን በማን ይቀናል? የተጎዳው ግን እጅግ የተጎዳው ግን የአምሀራ/አማራ ብሄር ነው። ያሳዝናል!

…… ይህ ብሄረሰብ እንዴትና ለምን ተጎዳ?! ~ እኔ ይሄን ጥያቄ በምን አቅሜ እመልሰዋለሁ። ነገር ግን ላለፉት 27 አመታት የሰማሁት የዚች ሀገር የፖለቲካ ስክሪፕት የተጻፈው በአማራ ብሄር ጥላቻ ላይ ተመርኩዞ ነው።….. አማራ ነፍጠኛ ነበር፣ ጨቋኝ ነበር፣ ገዢ መደብ ነበር፣ የራሱን በሌላው ላይ በሀይል የሚጭን አምባ ገነን ነበር፣ አማራ በቃ በጠቅላላው ጸረ-ኢትዮጵያ ብሄሮች ነበር።

……. 27 አመታት ይህን የጥላቻና የግፍ መዝሙር አልዘመርኩም የሚል ቢኖር እንኳ አልሰማሁም የሚል አለ ብዬ ላምን አልችልም። እኔ ግን በየስብሰባው መድረክ፣ በየፖለቲካ ውይይቱ፣ በየመፈክሩ ሲባል ሲነገር ሰምቻለሁ፣ አውቃለሁ።

አማራ ለየክልሎቹ ሁሉ አንዳች አስፈሪ ጭራቅ ተደርጎ ነበር!!!

አሁን “እንዴት የአንድ ሀገር ህዝብ ለሌላው ህዝብ ጠላት ተደርጎ ይሰበካል?” የሚል ጊዜ ያለፈበት ጥያቄና መላሾቹ በማስመሰል ካባ ውስጥ በገቡበት በዚህ ሰአት መጠየቅ ጅል ገልቱ ያስብላል እና አንጠይቅም። እናም ከጊዜው ጋር ማዝገም በሚለው መንገድ እንሂድ።

ምንም እንኳ ጊዜው በዘርና በብሄረሰብ ካልተደራጁ አቻ ምላሽ ለመመለስም ሆነ መልሶ ለማጥቃት የማይቻልበት ፈታኝ ወቅት እንደሆነ በቅጡ ብረዳውም የግል እምነቴ ነውና ከኢትዮጵያዊነቴ ውጪ የምደራጅበት ሌላ ቡድን የለኝም።

ነገር ግን አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ ራሱን መከላከል ብቻ ሳይሆን ታሪኩን ለማደስ ሲንቀሳቀስ “አይዞህ፣ በርታ!” ከማለት የሚያግደኝ አንዳችም ነገር የለም።

እንዲያውም አረፈደ ባይ ነኝ!!
አማራ አረፈደ!

27 አመት ከዛሬ ነገ ነገር ይቀየራል እያለ፣ ማንነቱን በማያከብሩና በማይቆሙለት እየተመራ?! በገዛ ሀገሩ “ሰፋሪ፣ ስደተኛ፣ ዛፍ ቆራጭ” እየተባለ? በስሙ እየተነገደ? ልጆቹ ይማሩበት ትምህርት ቤት፣ ሚስቱ ትወልድበት ጤና ጣቢያ ይሄድበት ሁነኛ መንገድ ተከልክሎ እዚያው በነበረበት እንዲቆይ 27 አመት ተቆልፎበት?…… ለምን አይደራጅ? እንኳን በአማራነት ሌላስ ስም ተደራጅቶ ለመብቱ ቢሟገት እንዴት ተው ይባላል?…..

ሀገር እኮ ሰው ናት! ተራራ ወንዙ ሜዳው ሸለቆውኮ ለመዝሙሩ እንጂ ኗሪውኮ ሰው ነው። ሰው ባገሩ መኖሩ ካልታወቀለት ምኑን ሀገር አለው?…..

አማራስ ይደራጅ! ይታገል! ይሟገት! …..ስሙን ያድስ፣ ……. እኔስ በብሄር ባልደራጅ አትደራጅ ላልል ቃል እገባለሁ! ፋኖ ግን ሂድ!!